ከሰላም እስከ ልማት – የባሕር ዳር ከተማ ጉዞ !

2
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “አርቆ ማየት አልቆ መሥራት” በሚል መሪ መልዕክት የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት እና የፓርቲ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክን አካሂዷል።
በብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን 2018 በጀት ዓመት በከተማዋ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት ዓመት ነበር ብለዋል።
በከተማዋ የተሠሩ የልማት ሥራዎች እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት የነዋሪዎችን ችግሮች የፈቱ እና በነዋሪዎችም ዕውቅና የተሰጣቸው መኾናቸውን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ በፓርቲ ሥራ ምርጫን በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁም ከፍተኛ ስኬት መኾኑን አውስተዋል።
2019 ያሉ ችግሮችን በመፍታት እና ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ባሕር ዳርን እና ነዋሪዎቿን የሚጠቅም ሥራ የምንሠራበት ይኾናል ነው ያሉት።
የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው 2018 ዓ.ም ከዕቅድ ጀምሮ እስከ በጀት ማጠናቀቂያ ሥራ በሥነ ምግባር እና በዕውቀት ለከተማዋ የወደ ፊት እጣ ፈንታ እና ለነዋሪዎቿ ጠቃሚ የኾኑ ተግባራት የተከናወኑበት ውጤታማ የበጀት ዓመት ነበር ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ባሕር ዳርን ሰላማዊ በማድረግ ስኬታማ ሥራ ተከናውነዋል ነው ያሉት። በኮሪደር ልማት፤ በኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት፣ በወጣትች የሥራ ዕድል ፈጠራ፤ በእንሰሳት ሀብት ልማት፤ በማኅበራዊ ልማት፤ በአገልግሎት ዘርፍ፤ በቱሪዝም እና በሌሎች ዘርፎች ከመቸውም ጊዜ በላይ ውጤታማ ሥራዎች የተከናወኑበት እንደነበር ነው የገለጹት።
በከተማዋ ወደ ኋላ የማይመለስ የኢኮኖሚ ልማት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በዚህ ሂደት በመንግሥት አመራሩ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መተሳሰብ እና መቀራረብ እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት።
በ2019 በጀት ዓመትም የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል። በተለይ የከተማዋን ሰላም አስጠብቆ በማስቀጠል ለኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleመሪዎች ባሳዩት ጽናት፣ ትዕግሥት እና ቁርጠኝነት ስኬታማ ሥራዎች ተሠርተዋል።
Next article‎በበጀት ዓመቱ ግልፅ፣ ተጨባጭ እና አካባቢያዊ ፀጋዎችን መሠረት ያደረገ እቅድ ይተገበራል።