
የሰሜን ጎጃም ዞን አሥተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው።
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ በየደረጃው በሚገኙ መሪዎች እና ባለሙያዎች መካከል የነበረው ቅንጅት የሕዝብን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል። በተለይም የጸጥታ ችግሮች በነበሩበት ወቅት መሪዎች ባሳዩት ጽናት፣ ትዕግሥት እና ቁርጠኝነት የምርጫ እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራዎች በስኬት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል። በጤናው ዘርፍ የማኅበረሰብ አቀፍ ፋርማሲ አገልግሎት መጀመሩን፣ በግብርናው ሰፋፊ የፍራፍሬ ኩታ ገጠም ልማት መተግበሩን እና የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም መጀመሩን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በዞን እና ወረዳ ደረጃ የተያዙ የመንገድ እና የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተዋል። ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሠብሠብ ዞኑ በክልሉ ከቀዳሚዎቹ አምስት ዞኖች ተርታ መሰለፉን ገልጸዋል።
የመልካም አሥተዳደር እና የጸጥታ ችግሮች በተሟላ ሁኔታ አለመፈታታቸው በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ክፍተቶች መኾናቸውን አመላክተዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማስተዋል አሰሙ በ2019 በጀት ዓመት የአሠራር ብክነትን ለማስቀረት “አንድ ዕቅድ እና አንድ ሪፖርት” ብቻ እንደሚተገበር ገልጸዋል። የዞን እና የወረዳ ዕቅዶች ከማዕከላዊ ዕቅድ ጋር ተጣጥመው እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት መሪዎች እና ባለሙዎች በተሻለ ዝግጅት እና ትጋት በመሥራት ዞኑን በክልሉ በአፈጻጸም ቀዳሚ ለማድረግ የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ባሕር ዳር #መስከረም_04/2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
