ድርቅን የሚቋቋሙ ስድስት አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ተለቀቁ።

5
🌾
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማላማድ እና በማባዛት የአርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል።
ኢንስቲትዩቱ በ2018 በጀት ዓመት ሰባት የሰብል ዝርያዎችን ለመልቀቅ ታቅዶ ስድስት ዝርያዎች ወደ አርሶ አደሮች መለቀቃቸውን የኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዓለማየሁ አሰፋ (ዶ.ር) ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የተለቀቁት አንድ የጤፍ፤ ሦሥት የበቆሎ፤ አንድ የሽንብራ እና አንድ የድንች ዝርያዎች በድምሩ ስድስት አዳዲስ ዝርያዎች መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
እነዚህ ዝርያዎች የዝናብ አጠር አካባቢዎችን መሠረት ያደረጉ ናቸው ብለዋል። በተለይም በመስኖ የሚለሙ፤ ሙቀትን የሚቋቋሙ፤ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ እና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ መኾናቸውንም አንስተዋል።
አሁን ላይ የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የለቀቃቸው ሦስት የበቆሎ ዝርያዎች ድርቅን እና አረምን መቋቋም የሚችሉ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ምርት የሚሠጡ እና ቀድመው የሚደርሱ ስለመኾናቸው ነው ያስረዱት። በተለይም እንደ ዋግኽምራ እና በለሳ ላሉ ዝናብ አጠር አካባቢዎች የሚስማሙ ናቸው ነው ያሉት። ሌላኛው እንደ ሀገር በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቀው የድንች ዝርያ ደግሞ 2 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሚደርስ፤ ምርታማነቱ ከፍተኛ የኾነ ዝርያ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ።
እነዚህ የምርምር ውጤቶች ተዋውቀው ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ሲደረጉ በዝናብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን የሚፈቱ እንደኾኑ ነው የተናገሩት።
ከዚህ ቀደም የብዕር ሰብል ዝርያዎች እንደ እንቁ ዳጉሳ እና መልካም ማሽላ የምርምር ውጤቶች ለማኅበረሰቡ በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ማድረጉን ነው ያነሱት። የማሾ የምርምር ውጤትም በግብይት ሥርዓቱ ላይ የኢኮኖሚ ምንጭ እየኾነ ይገኛል ብለዋል።
በተለቀቁት ቴክኖሎጂዎች እና ምርጥ ዘሮች አማካኝነት አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲኾኑ የማስተዋወቅ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ነው ያሉት። ኤሊኖን እና የዝናብ እጥረትን በዘላቂነት ለመቋቋም ግን ከአዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ዝርጋታ ጎን ለጎን የውኃ እቀባ ሥራዎችን አቀናጅቶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ዓመትም 14 አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ለመመርመር ማቀዱንም ገልጿል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየምሥራቅ ዕዝ ክፍለ ጦር ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
Next articleየ2019 ዓ.ም የሬሜዲያል መርሐ ግብር የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ይፋ ሆነ።