የኢኮኖሚ ካቴናውን መበጠስ ለነገው ትውልድ የነጻነት ስንቅ ነው።

7
ዛሬ ጳጉሜ 5 ነው። የ2018 ዓ.ም መገባደጃ፤ የ2019 ዓ.ም መሸጋገሪያ ዕለት። ዕለቱ በመላው ኢትዮጵያ “የነገው ቀን” በሚል መሪ መልዕክት በተስፋ እና በመልካም ምኞት፣ የሀገርን እና የትውልድን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ አሻግሮ በመመልከት ብሎም አሻራን በማሳረፍ እየተከበረ ይገኛል።
ነገን ማሰብ ዛሬን በትክክል ከመረዳት እና የትናንቱን ጠባሳ በአግባቡ ከመፈወስ ይጀምራል። ኹሉም ኢትዮጵያውያን በውል እንደሚረዱት ኢትዮጵያ መልስ የሚሹ ብዙ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት። እነዚህ ችግሮች በጊዜ ፈውስ የሚፈልጉ ለትውልድ መሸጋገር የሌለባቸው ናቸው።
ከእነዚህ መካከል አንዱ የብዙዎቹ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነው። እርሱም የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ነው።
ለዚህች ለምንኖርባት ታላቋ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ጂኦ ፖለቲካዊ ቅንጦት አልያም ተራ የንግድ አማራጭ ፍለጋ አይደለም። የሀገር ህልውና፣ የብሔራዊ ደኅንነት እና የኢኮኖሚ ነፃነት ማረጋገጫ ማዕከላዊ ምሰሶዋ እንጅ።
የነገዋን ብሩህ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የባሕር በርን በብርታት መክፈት ለነገው ትውልድ የማይታጠፍ ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ አደራ ነው። “ያሉት ከሚጠፋ፥ የወለዱት ይጥፋ” በሚሉት ኢትዮጵያውያን ዘንድ ደግሞ አደራ ሊከበር ግድ ይላል።
ይህንን የነገ ተስፋ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ታዲያ ያለፉትን ሦሥት አስርት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር ማሳለፏ ያስከተለባትን ሁለንተናዊ ኪሳራ ቆም ብሎ መመርመር የግድ ይላል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ካጣችበት ጊዜ ጀምሮ ያለፉት ዓመታት ጉዞዋ በከፍተኛ የኢኮኖሚ መታፈን፣ በጂኦ ፖለቲካዊ ተጋላጭነት እና የደኅንነት ስጋት የተሞላ ነው። ይህ የወደብ አልባነት በሀገሪቱ ላይ የፈጠረው የኢኮኖሚ እሥራት የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጎታል።
ይህ ወደ ቀይ ባሕር የመመለስ መሻቷ ከጎረቤቶቿ ጋር የጋራ ዕድገትን እና ቀጣናዊ ትስስርን ታሳቢ ያደረገ ነው። የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጧ ደግሞ ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ጥበቃ ታላቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይኾናል።
ታዲያ ኢትዮጵያውያን ወደ 2019 ዓ.ም መሸጋገሪያ የመጨረሻዋ ጳጉሜ 5 በ “የነገው ቀን” ላይ ቆመን ወደ ፊት ስንመለከት ኢትዮጵያን ከባሕር በሯ ጋር ማየት የግድ ይላል። ዛሬ ላይ ሁለንተናዊ ትግል በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ቀይ ባሕር መመለስ የነገዋን ኢትዮጵያ ቅርጽ ይወስናል።
የባሕር በር ባለቤትነትን እውን ማድረግ የዛሬው ትውልድ ለነገው ትውልድ የሚያስረክበው ትልቁ የነፃነት ስንቅ ነው። የነገው ቀን እውነተኛ ትርጉምም ኢትዮጵያ የባሕር በሯን አስከብራ እና የኢኮኖሚ ካቴናውን በጥሳ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚገባትን ቦታ ስትይዝ ብቻ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleእርስ በእርስ የመረዳዳት ባሕልን የሚያጠናክሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
Next articleበአማራ ክልል ከ 1 ሺህ 200 በላይ ለሚኾኑ ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ።