
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በ 2019 አዲስ ዓመት በክልሉ ይቅርታ የተደረገላቸውን ታራሚዎች አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የክልሉ መሥተዳደር ምክር ቤት ጳጉሜ 4/2018 ዓ.ም ባካሄደው ሰባተኛ ዙር አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ በሁለተኛ ዙር ይቅርታ ሊደረግላቸው ይገባል የተባሉ የሕግ ታራሚዎችን አስመልክቶ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል።
በዚህ መሠረትም ወንድ 1 ሺህ 169፤ ሴት 33 በድምሩ 1 ሺህ 202 ታራሚዎች ከጳጉሜ 4/2018 ዓ.ም ጀምሮ በይቅርታ እንዲፈቱ የክልሉ መሥተዳደር ምክር ቤት ወስኗል ነው ያሉት።
የይቅርታ ተጠቃሚ የኾኑ ታራሚዎች ይቅርታውን ሊያገኙ የቻሉባቸውን ምክንያቶች ሲጠቅሱ፦
ከተበዳይ ወገን ጋር እርቅ መፈጸም ያልፈለጉ፤ ለተበዳይ ወገን ካሣ ለመክፈል ፈቃደኛ ያልኾኑ፤ የእሥራት ቅጣታቸውን ያልጨረሱ እና በጾታዊ ጥቃት ተከሰው ፍርድ ያገኙ ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ አልኾኑም ነው ያሉት።
የክልሉ መሥተዳደር ምክር ቤት በጸጥታ ችግር ውስጥ ኾኖም ይህን ውሳኔ ማሳለፉ ለዜጎች መብት ጥበቃ ያለውን አርቆ አሳቢነት ያሳየ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ሰዎች ከጥፋታቸው መማር የሚችሉ መኽናቸውን ከግንዛቤ ውስጥ ያስባ መኾኑን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥት ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ወደ ኅብረተሰቡ ሲገቡ ለክልሉ ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ የራሳቸውን ሚና እንደሚወጡ እምነት አሳድሮ የይቅርታ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ውሳኔ ማስተላለፉን ተናግረዋል።
በይቅርታ ወደ ኅብረተሰቡ የሚቀላቀሉ ታራሚዎች በርግጥም የታረሙ እና የባሕሪ ለውጥ ያመጡ መኾናቸውን ለክልሉ ሰላም መረጋገጥ በመሥራት፤ የወንጀል አስከፊነትን በማስተማር እና በሌሎች በጎ ተግባራት በመሳተፍ ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
