እርስ በእርስ የመረዳዳት ባሕልን የሚያጠናክሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

3
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞች እና ለተማሪዎች ልዩ ልዩ ድጋፎችን አድርጓል። ለ100 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የዘይት እና የዱቄት ስጦታ አበርክቷል።
ወላጆቻቸውን ላጡ እና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎችም የደብተር እና የስክሪብቶ ድጋፍ ተበርክቷል። የአልባሳት ድጋፍ እና የደም ልገሳ መርሐ ግብርም ተከናውኗል።
የበዓል መዋያ ድጋፉ የተደረገው ከከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች እና አጠቃላይ ሠራተኞች ሃብት በማሠባሠብ፣ ከሥራ ማስኬጃ በጀት በመቀነስ እንደኾነ የግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ገልጸዋል።
ይህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደስተው እንዲውሉ ዓላማ ማድረጉን ጠቁመዋል። ግብርና አምራች ተቋም ነው ያሉት ኀላፊው ያለውን መሬት፣ ጉልበት እና ውኃ በአግባቡ በመጠቀም ምርትን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑን ገልጸዋል።
ከተቋሙ መደበኛ ተግባር ባሻገር በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ሰፋፊ ሰብዓዊ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል። ከእነዚህም መካከል በባሕር ዳር ከተማ በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ አምስት አቅመ ደካሞች አዲስ ቤት መገንባት እና ማደስ ይገኙበታል።
እርስ በርስ የመረዳዳት ባሕልን የሚያጠናክሩ እና ለተተኪው ትውልድ ተስፋ የሚሰጡ እነዚህ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
ቢሮው ያዘጋጀውን ለ120 ተማሪዎች የሚኾን የትምህርት ቁሳቁስ እና የአልባሳት ድጋፍ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ተረክቧል። ድጋፉን የተረከቡት የመምሪያው ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ቢሮው በከፍተኛ ተነሳሽነት ከሚያከናውነው የማዕድ ማጋራት ተግባር ባለፈ በበጎ ፈቃድ የክረምት ሥራዎችም ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መኾኑን አድንቀዋል።
ሌሎች ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ባለሃብቶች ይህንን በጎ ተግባር አርዓያ በመከተል ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ እና የተቸገሩ ወገኖችን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማ ጉዞ
Next articleየኢኮኖሚ ካቴናውን መበጠስ ለነገው ትውልድ የነጻነት ስንቅ ነው።