የአማራ ክልል ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ቴክኖሎጂ እንዲኾን እየተሠራ ነው።

9
ቴክኖሎጂ የዓለምን ገጽታ ቀይሯል፤ ግብይቶች፤ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች፤ የመሠረተ ልማት ጥበቃዎች እና የሰውን ልጅ ድካም የሚያቀሉ ቴክኖሎጂዎች በእጅጉ ተራቀዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ደግሞ የዓለምን ዕይታ ቀይሯል። በሕክምናው ዘርፍ እገዛ የሚያደርጉ፤ የግብይት ሥርዓትን የሚያሳልጡ፤ የሀገርን ደኅንነት የሚያስጠብቁ፤ የሳይቨር ደኅንነትን የሚጠብቁ ቴክኖሎጂዎች የዓለምን ጉዞ ቀይረዋል።
ኢትዮጵያም ትውልዱን ለመቅረጽ እና ውጤታማ ለማድረግ በዲጂታል 2030 ለቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረትን ሰጥታለች። በቴክኖሎጂው ዘርፍ በዓለም ተወዳዳሪ ለመኾን በትኩረት እየሠራችም ነው።
የአማራ ክልልም በ25 ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅዱ ላይ ልዩ ትኩረት ለቴክኖሎጂ ሰጥቷል። በቴክኖሎጂ የታገዘው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት አንዱ ማሳያ ነው።
በክልሉ የተቋቋመው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ የክልሉን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሳደግ፤ የማኅበረሰቡን የቴክኖሎጂ ንቃተ ኀሊና ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ ይገኛል።
ተቋሙ አገልግሎት ሰጭ እና አገልግሎት ፈላጊው በዲጂታል ሥርዓት እንዲግባቡ፤ ቴክኖሎጂን አውቀው እና ተረድተው እንዲጠቀሙ፤ የአገልግሎት አሠጣጥ ችግሮች እንዲቀረፉ፤ ተቋማት በቴክኖሎጂ እንዲዘምኑ ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ነው።
የአማራ ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ምክትል ቢሮ ኀላፊ የቻለ ይግዛው በክልሉ ከ35 በላይ የዲጂታል መፍትሔዎች ለምተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።
የለሙ ሲስተሞች የሕዝብን አገልግሎት ያሳልጣሉ፤ የመንግሥትን አገልግሎት የመሥጠት አቅም ያሳድጋሉ፤ የዲጂታል ኢኮኖሚን ይደግፋሉ ነው ያሉት።
ቢሮው በክልሉ ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውጤታማ ተግባርን አከናውኗል። ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለኾኑ ዜጎች የኢትዮ የኮደርስ ሥልጠና ሠጥቷል። ከ12 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት እንዲኾኑ በትኩረት እየሠራም ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ “ኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሠረት” በሚል መሪ መልዕክት ዐውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት ባደረገበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በክልሉ “ዲጂታል አማራ” በሚል በ25 ዓመቱ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ላይ ቴክኖሎጅ እንደ ልማት መዳረሻ መፍጠሪያ ተደርጎ ተይዟል ነው ያሉት።
በ25 ዓመቱ ስትራቴጅክ ግብ ላይ በ2042 የአማራ ክልል ዋነኛ ሃብት፤ የአገልግሎት መስጫ እና የኢኮኖሚ የዕድገት ምንጭ ቴክኖሎጂ እንዲኾን እየተሠራ ነው ብለዋል። በክልሉ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምድ ዕድገት እያሳየ መጥቷል ነው ያሉት።
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የመንግሥት ተቋማት ከወረቀት አሠራር ወጥተው ወደ ዘመናዊ የዲጂታል አሠራር እየተሸጋገሩ መኾኑን ተናግረዋል። ከ49 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት በመኾን፤ ዜጎች በቴሌ ብር እና በባንኮች በዲጂታል መድረኮች በመገበያየት፤ በመሶብ አገልግሎት ፈጣን ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት።
ወጣቶች በእጃቹህ የያዛችሁት ስማርት ስልክ መዝናኛ ብቻ ሳይኾን የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት በመኾኑ በአግባቡ ልትጠቀሙበት ይገባልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበጋራ ልማት እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደ ነገ እንሻገራለን።
Next articleየነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ…