የነገዋን ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ…

8
➡️🚀
በየዕለቱ ተለዋዋጭ በኾነው የዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ የቴክኖሎጂው ተጽዕኖ ፈጣሪነት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል። በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት(ኤ አይ) የዓለምን ሁለንተናዊ ገጽታ እየቀየረ የመጣ የዘመኑ ክስተት ኾኗል።🌍
ኢትዮጵያም ይህንን ተለዋዋጭ የበዛበት የቴክኖሎጂ ለውጥ መሠረት ያደረገ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማትን ትኩረት አድርጋ እየሠራችበት ትገኛለች። ለዚህም ቀደም ባሉት ዓመታት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች።
🎯 ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጅን በመተግበር ላይ ትገኛለች። ይህንን እያሳለጡ የሚመሩ የሳይንስ ሙዚዬም፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዮትን እና ሌሎችንም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ተቋማትን አደራጅታለች።
የመጭውን ዘመን የቴክኖሎጂ ተጽዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ለነገው ተወዳዳሪነቷ መሥራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በተለይም ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መኾኗን ተናግረዋል። ወጣቶችንም ነገ ለሚጠብቃቸው ውድድር ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል። በዚህም ትውልድ ላይ መሥራት ታሳቢ አድርጋ እየሠራች መኾኗን ገልጸዋል።
ይህንን መሠረት በማድረግ በዓለም ሁለተኛውን በአፍሪካ ደግሞ የመጀመሪያ የኾነውን የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ እየገነባች መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በአንድ ዓመት ውስጥ ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምር መናገራቸው ይታወሳል። ይህም በሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
ዩኒቨርሲቲው ሥራ ሲጀምር ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የኤ አይ ስኮላርሽፕ የትምህርት ዕድልን እንደሚፈጥር እና ለአፍሪካውያን ትልቅ የቴክኖሎጂ መሠረት ኾኖ እንደሚያገለግልም ጠቁመዋል። 🎓🤝
የሰው ሠራሽ አስተውሎት በተለይም ለኢትዮጵያ ለሀገር በቀል ዕውቀት ግንባታ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለቁልፍ የልማት ዘርፎች ዕድገት ማሳለጫ፣ ለምጣኔ ሃብት እና የፈጠራ አቅምን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና አለው።
በኢትዮጵያ የሚገነባው ዩኒቨርሲቲም ከትምህርት ባለፈ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸውን ወደ ሥራ የሚቀይሩበት ማዕከልም እንደሚኾን ይጠበቃል።
የዲጂታል ኢኮኖሚውን የሚያነቃቁ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚፈልቁበት ምኅዳርን ይፈጥራል። ይህም ለበርካታ ወጣቶች ልዩ የሥራ ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው።
ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት የነገዋን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል እንድትኾን እንደሚያደርግም ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየአማራ ክልል ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ቴክኖሎጂ እንዲኾን እየተሠራ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ቀዳማዊት ዝናሽ ታያቸው ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር አብሮ በመሆን «ተስፋን እንትከል»