
የምሥራቅ ዕዝ ኮር የሠራዊት አባላት በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሠላም ከተማ ለሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ። የኮሩ የጥገና ኀላፊ ኮሎኔል አበራ ጥሩ እንደገለጹት የኮሩ ስታፍ የሠራዊቱ አባላት ሀገራዊ ግዴታቸውን ከመወጣት ባለፈ ከወርሃዊ ደመወዛቸው ላይ በመቀነስ ለአካባቢው ተማሪዎች 33 ደርዘን ደብተር እና እስክሪብቶ ድጋፍ አድርገዋል።
ድጋፉ ተማሪዎች በቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸዉ እንዳይሰናከሉ እና በሙሉ የሥነ ልቦና ዝግጅት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማስቻል መኾኑንም ኀላፊው ተናግረዋል። ሠራዊቱ ሀገርን እና ሕዝብን ከመጠበቅ ባለፈ ማኅበረሰቡን በሚጠቅሙ ልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ በቁርጠኝነት እየተሳተፉ መሆኑን አብራርተዋል።
የፍኖተ ሠላም ከተማ አሥተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደረጀ ታደሰ ሠራዊቱ የሕዝብን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን ለተማሪዎች ያደረገውን ሁለገብ ድጋፍ አድንቀዋል።
የሠራዊቱ አባላት ላሳዩት መልካም አርአያነት እና ሰብዓዊ ደግነት በከተማው ሕዝብና በትምህርት ባለድርሻ አካላት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
መረጃው የምሥራቅ ዕዝ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
