ምርት በገበያው በሚፈለገው መጠን ስለገባ ሕዝቡ ተረጋግቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት ሊፈጽም ይገባል።

19
በዓል ሲመጣ በየቤቱ ሸር ጉዱ አለ። አቤት የገበያው ግርግር፣ የገበያው ሁካታ፣ የበጉ፣ የፍየሉ እና የዶሮ ድምጽ ተደራርቦ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ቀለሙን ቀይሮ አዲስ ድባብን ይፈጥራል።
የጨፌው ሽታ፣ የክት እና የአዲስ ልብስ ዝግጅት፣ የቤት ውስጥ ማስተካከያው ራሳቸውን ችለው ትልቅ ድባብ ናቸው። አዲስ ዓመት ሲመጣ በእያንዳንዳችን ቤት ውስጥ የሚገባው ደስታ ሕይወታችንን በታደሰ ተስፋ እና በሐሴት ያጥለቀልቀዋል።
​በዚህም የዘንድሮው የአዲስ ዓመት የበዓል ገበያ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ጭማሪ መኖሩን በተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
በዓልን ሰበብ በማድረግ በሕገ ወጥ መንገድ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት። በዓል የደስታ እንጂ ዋጋ የሚጨመርበት አይደለምም ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኅላፊ አትክልት ሀሳቤ ለአዲስ ዓመት የበዓል ግብይት የተረጋጋ እንዲኾን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። ቢሮው ከግብርና፣ ከሥራ እና ክህሎት፣ ከእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ቢሮዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የገለጹት።
በተለይም የምርት አቅርቦቱን በመለየት ምርቱ የአካባቢ ገበያዎች፣ የእሑድ እስከ አሑድ ገበያዎች እና ሁለተኛ ደረጃ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ተደራሽ የማድረግ ሥራ መሠራቱን አንስተዋል። አምራቾችም በቂ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ መቻላቸውን ተናግረዋል።
​በነፃ ገበያ ከሚቀርቡት ውጭ በተደራጁ አካላት እና ብዛት ምርት ባላቸው ግለሰቦች አማካይነት ከ700 ሺህ በላይ የዕርድ እንስሳት፣ የደለቡ ሰንጋዎች፣ ፍየሎች እና በጎች ለገበያ ቀርበዋል ብለዋል።
ይህም በየቀኑ እየጨመረ የሚሄድ እንደኾነ ነው የጠቆሙት። ከ2 ሚሊዮን በላይ የሥጋ ዶሮዎች ተዘጋጅተው ለገበያ እየቀረቡ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
በወተትም ከ34 ሚሊዮን ሊትር በላይ ወተት በተደራጁ አካላት አማካኝነት ለኅብረተሰቡ እየቀረበ ነው ብለዋል። ዘይት በአምራች ኢንዱስትሪዎች በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርቡ እየተደረገ እንደኾነም አስረድተዋል። የምርት ክምችት ካለበት ወደ ሌለበት የገበያ ትስስር ቀድሞ መሠራቱንም ነው የገለጹት።
​በሌላ በኩል በሁለተኛ ደረጃ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትም ዘይትን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችም በተሻሻለ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት እየተፈፀመ ነው። ይህም ለሸማቹ ማኅበረሰብ እፎይታ የሚሰጥ መኾኑን አስረድተዋል።
አትክልት እና ፍራፍሬ ሽንኩርት እና ድንችን ጨምሮ ለበዓሉ አስፈላጊ የኾኑ አትክልቶች በበቂ መጠን እንዲቀርቡም ተደርጓል። ​ስኳር ከጣና በለስ ጭምር ቀጥታ እንዲገባ በማድረግ እየቀረበ ነው ብለዋል።
የበዓል ግብይትን የተረጋጋ ለማድረግ የድንኳን ገበያዎች ጭምር አገልግሎት በመስጠት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ተሠርቷል ያሉት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ማኅበረሰቡ ተረጋግቶ ግብይት መፈፀም እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
​ቢሮው የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት ባለፈ በበዓል ወቅት የሚፈጠር የገበያ አለመረጋጋትን ለመከላከል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑም ተመላክቷል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ምንዳን እንጅ ዕዳን አታወርስም፡፡
Next articleሰላማን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ለበጎነት የተዘረጉ የሠራዊቱ እጆች በፍኖተ ሰላም