ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ምንዳን እንጅ ዕዳን አታወርስም፡፡

7
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጳጉሜን አምስት የነገውን ቀን አስመልክቶ መልዕክት አስተላልፏል። በመልዕክቱም ኢትዮጵያ ነገዋን ዛሬ እየሠራች ነው ብሏል።
ነገ የሚወሰነው ዛሬ በምንሠራው ሥራ ነው። የነገ ስኬታችን የሚቀረጸው በዛሬው ጥረታችን ነው። ከትናንት መልካም ልምዶችን በመቅሰም፣ ዛሬን በትክክል አጢኖ የነገን ራዕይ ዛሬ ላይ ኾኖ መገንባት የመንግሥታችን ጽኑ እምነትና መለያ ባሕሪ ነው።
ሀገር በቀል ዕውቀትን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አስተሳስሮ ነገን ለመዋጀት መዘጋጀት ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት እንደኾነ መንግሥት በፅኑ ያምናል፡፡ ለዚህም ነው ዲጂታላይዜሽንን እንደ አስቻይም እንደ ኢኮኖሚ ዘርፍም በመውሰድ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ያለው፡፡
ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ ምንዳን እንጅ ዕዳን አታወርስም፡፡ ጊዜ በየአንጓዉ ለሚጠይቀዉ ጉዳይ ምላሽ መስጠት አለመቻል የትውልድ ዕዳ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሀገራችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ታዳጊዎችን በትምህርት ቤት እየመገበች የምታስተምረው፤ ለዚህም ነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን በነጻ የኮደርስ ሥልጠና እያበቃች ያለችው፤ ለዚህም ነው የመጀመሪያውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ እያቋቋመች ያለችው ፡፡ ነገ ያለቴክኖሎጂ ዕውቀት፣ ነገ ያለሳይበር ደኅንነት፣ ነገ ያለመረጃ ሉዓላዊነት የሕልውና አደጋ አንደኾነ መንግሥታችን ይገነዘባል፤ ትውልዱን ለዚያ ያዘጋጃል፡፡
ለዘመናት ኋላቀር ሲባል የነበረዉ የኢኮኖሚ ዘርፍ ግብርና ነገ ያለቴክኖሎጂ ሕልውናዉ አደጋ ላይ ነው፡፡ ለተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ቅድመ ጥንቃቄ እና ምላሽ አሰጣጥ ዲጂታላይዜሽን ወሳኝ ነው፡፡ የመንግሥት አገልግሎቶችን በጥራት እና በፍጥነት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ያለፉት ዘመናት አሠራሮች አይደለም ነገ ዛሬም አዋጭ አይደሉም፡፡
በዓለማቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለማፍራት ዲጂታል ክሕሎት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለእነዚህ ኹሉ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ስለምትገኝ ነው “ኢትዮጵያ ነገዋን ዛሬ እየሠራች ነው” የምንለው፡፡
የጳጒሜን አምስተኛ ቀን የነገ ቀን ብለን ማክበራችንም መጪዉ ዘመን የቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነትን የሚጠይቅ፣ መረጃ ትንተና ላይ የተመሠረተ ውሳኔ የሚሰጥበት፣ ከግብርና እስከ ሕዋ ሳይንስ ምርምሮች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ የሚኾኑበት ዘመን ዋዜማ ላይ ስለምንገኝ ለዚያ የሚመጥን ትውልድ ለማፍራት እንደምንሠራ ለማስገንዘብ ነው፡፡
ጳጉምን አምስት የነገ ቀን በሚል ስያሜ መከበሩ ዲጂታላይዜሽን ለነገዋ ኢትዮጵያ ግንባታ እና ሉዓላዊነት መከበር ሀገራችን ወደ ዲጂታላይዜሽን ሽግግር ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ለማብሰር ነው፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleሕንጻ ከመሠረት፤ ትውልድ ከልጅነት መታነጹ ነገም ያማረ ይኾናል።
Next articleምርት በገበያው በሚፈለገው መጠን ስለገባ ሕዝቡ ተረጋግቶ በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት ሊፈጽም ይገባል።