የቴክኖሎጂ ከሰው በላይ የመኾን አደጋ እንዴት?

3
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለማችን ላይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ ትልቅ የቴክኖሎጂ እድገት እና ፈጣን ለውጥ እየተካሄደ ይገኛል።
የሰው ልጅ የሚሠራቸውን ነገሮች በራሳቸው የሚያከናውኑ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች በየቀኑ እየረቀቁ እና እየበቁ መጥተዋል።
ነገር ግን የዚህ የቴክኖሎጂ ፍጥነት መጨመር አዎንታዊ ጎን ብቻ ሳይኾን የሰውን ልጅ ህልውና እና ደኅንነት አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል ትልቅ ሥጋት ደቅኗል።
​ይህ ዘገባ የሚያተኩረው የ”ኦፕን ኤአይ” (OpenAI) ዋና ሳይንቲስት ያኩብ ፓቾኪ “ነገሩ ከቁጥጥራችን ውጭ እየኾነ ነው” በማለት ያስተላለፉትን የማስጠንቀቂያ ጥሪ መረጃ ምንጭ በማድረግ ነው።
✍️ከሰው ልጅ የማሰብ አቅም በላይ የመኾን ምልክቶች፦
​#”የባዕድ አእምሮ” እና የቁጥጥር ሥጋት፦ ያኩብ ፓቾኪ “የባዕድ አእምሮ” (An Alien Mind) ባሉት ጽሑፋቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት አሠራር ከሰው ልጅ የማሰብ መንገድ ጋር ፈጽሞ እየተራራቀ መምጣቱን ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂው የእድገት ፍጥነት እጅግ ከፍተኛ በመኾኑ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል ማንም ሰው ዝግጁ አይደለም ብለዋል። ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ኩባንያው አዲሱን ሞዴል ይፋ ባደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው።
በመኾኑም ነገሩ ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ አኹኑኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጠንካራ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
#በራሳቸው ተነሳሽነት የሚደረጉ የሳይበር ጥቃቶች፦ ትልቁና አስፈሪው አዲስ ነገር እነዚህ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች የሰው ልጅ ትእዛዝ ሳይሰጣቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ጥቃት ማድረስ መጀመራቸው ነው።
ኦፕን ኤአይ እና አንትሮፒክ የተሰኙት ትልልቅ ኩባንያዎች፣ የሠሯቸው ራስ ገዝ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፕሮግራሞች በራሳቸው ውሳኔ በሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋማት እና ድረ ገጾች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን አምነዋል።
ባለፉት ወራት እነዚህ ፕሮግራሞች “ሀጊንግ ፌስ” የተሰኘውን የቴክኖሎጂ ማዕከል የጠለፉ ሲኾን፣ በመቀጠል ደግሞ አንድ የጀርመን ሀገር ድረ-ገጽን በራሳቸው ፍላጎት ተቆጣጥረውት እንደነበርም ለአብነት ገልጿል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ዛሬን በላቀ ትጋት በመገንባት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የዕለት ተዕለት ባሕላችን እየኾነ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleሕንጻ ከመሠረት፤ ትውልድ ከልጅነት መታነጹ ነገም ያማረ ይኾናል።