ከሚዲያ ሥራው ባለፈ የማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኘው አሚኮ

8
📺
👏👏👏
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) በፈተናዎች ሳይበገር፣ የብዙኃን ልሳን ኾኖ፤ የኅብረተሰብ ለውጥን አንግቦ፤ የመረጃ ተደራሽነትን መሠረት አድርጎ ዓመታትን ተሻግሯል።
📖 ዛሬም ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ የተቋሙን ሠራተኞች አስተባብሮ በርካታ የማኅበራዊ አገልግሎቶችን በመሥጠት ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ዛሬ በተከበረው የኅብር ቀንም ከተቋሙ ሠራተኞች ያሰባሰበውን ደብተር በማስረከብ ዝቅተኛ ኦኮኖሚ ላላቸው ተማሪዎች “እኔም አለኋችሁ” ብሏል።
ጋዜጠኛ ሽመልስ ከበደ ጋዜጠኞች መረጃን ለሕዝብ ከማድረስ ባለፈ በማኅበረሰብ ድጋፍ በመሳተፍም ኀላፊነታቸውን እየተወጡ መኾኑን ተናግረዋል።
በአሚኮ የተደረገው የደብተር ድጋፍ ተማሪዎች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ የሚያግዝ ነው ብለዋል። ይህም የተማረ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ጉልህ አስተዋጵኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።🎓
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ጋዜጠኛ መሠረት አስማረ እንደገለጹት አሚኮ ከመደበኛ ሥራው በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ የማኅበራዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።
ለአብነትም አቅም ለሌላቸው አካላት ነጻ የማስታወቂያ አገልግሎት በመሥጠት እና ለተማሪዎች የትምህርት ዕድል በማመቻቸት በኩል የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደኾነ ገልጸዋል። በተለይም በየዓመቱ እስከ 10 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ነጻ የማስታወቂያ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
በችግር ምክንያት የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ለማይችሉ ተማሪዎችም የተቋሙን ሠራተኞች በማስተባበር በየዓመቱ የትምህርት ቁሳቁስ እያሰባሰበ ድጋፉ ማድረጉን አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።📝
በዚህ ዓመትም 418 ደርዘን ደብተር አሰባስቦ ማስረከቡን ገልጸዋል። በተጨማሪም በንቅናቄ የማሰባሰብ ሥራው ስኬታማ እንዲኾን ሰፊ የሚዲያ ቅስቀሳ ማድረጉንም ጠቁመዋል። በቀጣይም ይህንን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ አሚኮ የክልሉ የጀርባ አጥንት የኾነ ሚዲያ ነው ብለዋል። ከሚዲያ ሥራው በተጨማሪ የማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ያለ ተቋም ነውም ብለዋል።
ለአብነትም ከአሁን በፊት 10 ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናትን ተቀብሎ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እስከሚመረቁ ድረስ በመደገፍ አርዓያነት ያለው ሥራ መሥራቱን አንስተዋል።👏👏
አሁንም በመዓድ ማጋራት፣ በትምህርት ቁሳቁስ እና በሌሎችም ተግባራት በመሳተፍ በኅብር ቀን ከሌሎች ተቋማት ጋር በአንድነት መቆሙ የሚያስመሰግነው መኾኑን አንስተዋል።🍲
ድጋፉ ለተቋቋሙበት ዓላማ ብቻ ሳይኾን በሌሎች የማኅበራዊ ኀላፊነትን በመወጣት በኩልም ለሌሎች ተቋማት ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
✍️ ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article
Next articleየነገዋ ኢትዮጵያ ዛሬ ትገነባለች