7
ሀገራዊ ኅብር የኢትዮጵያውያን የጋራ ማኅተም እና የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተምሳሌት በኾነው የዓድዋ ድልም ይገለጻል። በዳግማዊ አጼ ምኒልክ እና በንግሥት ጣይቱ መሪነት በ1888 ዓ.ም በተካሄደው ጦርነት የኢትዮጵያ ጀግኖች ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር በዓድዋ ተራራዎች ላይ ድል ያደረጉት ኅብረት ስለነበራቸው ነው።
የአንጸባራቂ ድሉ የአሸናፊነት ምስጢር በልዩነቶች ላይ የገነነ፣ ድንበር እና ቋንቋን የተሻገረ ፍጹም ሀገራዊ ኅብር ነው። ሁሉም ሀገር አትደፈርም ብሎ በመነሳቱ ዓድዋ ልዩነቶች የጥንካሬ ምንጭ ኾነው ያስገኙት ድል ተደርጎ ይቆጠራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያውያን በባሕል፣ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በፖለቲካ እና በእምነት የተለያየ ማንነት ቢኖራቸውም ዓድዋ የጋራ አንድነታቸውን እና ኅብረ-ብሔራዊ ማንነታቸውን በግልጽ ያሳየ ታሪክ መኾኑን መስክረዋል።
ጣሊያኖች በልዩነቶቻችን ላይ በመሥራት እና ኢትዮጵያውያንን በማዳከም ቅኝ ግዛት ለመጫን አቅደው መምጣታቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን ግን በሀገራቸው፣ በሉዓላዊነታቸው እና በነጻነታቸው ጉዳይ የማይደራደሩ መኾናቸውን ዓድዋ ሕያው ምስክር መኾኑን ተናግረዋል።
የዓድዋ የኅብር ኀይል ምን ያህል ተአምራዊ እንደኾነ ለትውልድ ሁሉ የሚሰብክ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የቅኝ ግዛት ወረራ ዘመን ነፃነቷን አስከብራ እንድትኖር ያደረገ፣ በላብ እና በደም የተጻፈ ሕያው መጽሐፍ ነው።
በጦርነቱ ወቅት የታየው የአባቶች እና የእናቶች የአንድነት እና የብዝኀነት ውበት ዛሬ በኅብር ቀን ለሚከበረው የኢትዮጵያዊነት ትሥሥር ጥንካሬ ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው።
ዓድዋ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን አስወግደው በኅብረት ሲቆሙ የማይበገሩ መኾናቸውን ያሳየ አኩሪ የታሪክ አሻራም ነው።
የዘመኑ ፈተና የውጭ ጠላት ብቻ ሳይኾን የውስጥ መቃቃር በመኾኑ ዛሬ ላይ የሚፈለገው ኅብር ራስን ከራስ ጋር የማስታረቅ የጠለቀ ጥበብን የሚጠይቅ ነው። የዓድዋን አኩሪ ታሪክ እንደ መማሪያ በመውሰድ ልዩነቶችን እንደ ግድግዳ ሳይኾን እንደ ጠንካራ ድልድይ መጠቀም የዘመኑ ትውልድ ትልቁ ኀላፊነት ነው።
ሀገራዊ ኅብር ዛሬም እንደ ትናንቱ ከልዩነት ኅብረ-ቀለም የሚፈልቅ የተስፋ እና የጥንካሬ ሕያው ዜማ ኾኖ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሊቀነቀንም ይገባል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢትዮጵያ – የኅብረብሔራዊነት ታላቅ ቤት!
Next articleከሚዲያ ሥራው ባለፈ የማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ የሚገኘው አሚኮ