ኢትዮጵያ – የኅብረብሔራዊነት ታላቅ ቤት!

8
ኢትዮጵያ እንደ አንድ ታላቅ ቤት ናት። ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህች ሰፊ እና ውብ ቤት ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕሎች፣ ታሪኮች፣ ሃይማኖቶች እና ማኅበራዊ ልምዶች ያሏቸው የብዙ ሺህ ዓመታት ቤተሰቦች ናቸው። አንድ ማዕድ የሚጋሩ፤ በአንድ ጣሪያ ሥር የሚጠለሉ፤
የአንዱን ሕመም ሌላው የሚታመም፤ የአንዱ ስኬት ለሌላው ኩራት የሚኾን የደም እና የአጥንት ትስስር ያላቸው የጋራ ማኅበረሰቦችም ናቸው።
እነዚህ የተለያዩ መገለጫዎች ያሏቸው እና አንድነታቸውን እንደ አለት ያጠነከሩ ሕዝቦች የሚኖሩባት ቤት ግንባታዋ ቀላል አልነበረም።
ልዩነቶች የቤቱ ውብ ቀለማት ናቸው፥ እንደ የአንድ አባት እና እናት ልጆች ኹሉም የየራሳቸው የፊት መልክ፣ ቋንቋ እና የኑሮ ዘይቤ አላቸው። ይህ ልዩነት ግን የቤቱን ማገር የሚያላላ አይደለም። ይበልጥ የሚያስውብ፣ የሚያደምቅ እና ጠንካራ የሚያደርግ የኅብር ጌጥ ነው።
ይሁን እና ይህችን ታላቅ ቤት ከውጭም ከውስጥም ሊያፈርሱ እና ቤተሰቡን ሊያናጉ የሞከሩ የፈተና አውሎ ነፋሶች ነፍሰውባታል። አንዳንዴ በመካከላቸው አለመግባባቶች ተፈጥረዋል፣ መገፋፋት እና መከፋፈል ጥላ አጥልቶባቸው አልፏል። ይህ ኹሉ ኾኖ ግን የዚህች ቤት ቤተሰቦች ለአንድም ቀን የቤታቸውን ሉዓላዊነት አሳልፈው ሰጥተው አያውቁም።
ስለዚህ ዛሬ ጳጉሜን 4 “የኅብር ቀን” ላይ ስንቆም ዋናው ጥያቄያችን መኾን ያለበት ያለን ብዝኅነት ብቻ ሳይኾን ብዝኀነታችንን እንዴት ወደ የጋራ አቅም እንለውጠዋለን? የሚለው ነው።
የፌደሬሽን ምክር ቤት የኅብር ቀን አስመልክቶ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት ኅብር ማለት ልዩነቶች ባሉበት ሁኔታ በእኩልነት እና በመከባበር በአንዷ ታላቅ ቤት ኢትዮጵያ የጋራ ሕይወትን መገንባት ማለት ነው ብሏል።
ማንነቶችንም ማክበር እንደሚገባ ኹሉ የጋራ እሴቶችንም ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያለው። መተሳሰብ፣ መቻቻል፣ መረዳዳት፣ የጋራ ጥቅምን ማስቀደም እና ልዩነቶችን በውይይት መፍታት የኅብር መሠረቶች መኾናቸውንም ጠቅሷል።
የኅብር ጥንካሬ የሚለካው ልዩነቶች በሌሉበት ሳይኾን ልዩነቶች ባሉበት ሁኔታ በሰላም እና በመተማመን አብሮ መኖር በመቻል ነው ያለው ምክር ቤቱ ይህም የአንድ ቀን ወይም የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ አይደለም። በየዕለቱ በአመለካከታችን፣ በንግግራችን እና በተግባራችን የምንገነባው የጋራ ኀላፊነት ነው ብሏል።
የሌላውን ማንነት ማክበር፤ የተለየ አመለካከትን ለመስማት ዝግጁ መኾን፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት መፍታት፤ ከፋፋይ ንግግርን መቃወም እና የጋራ ጥቅምን ማስቀደም ኅብርን ከሀሳብ ወደ ተግባር የሚያወርዱ መንገዶች መኾናቸውን ገልጿል።
በዚህም ኅብር ከአብሮነት ባሻገር ወደ የጋራ ኀላፊነት ይሸጋገራል ነው ያለው። የሀገር ሰላም እና ልማት የአንድ ሰው፤ የአንድ ቡድን ወይም የአንድ ተቋም ኀላፊነት ብቻ ሳይኾን የሁላችንም ተሳትፎ እና ኀላፊነት ሲኾን ኅብር ዘላቂ ይኾናል ብሏል ፌዴሬሽኑ በመግለጫው።
ኢትዮጵያ የተለያየ ቀለም ያላቸው እጆች ተሳስረው የሠሯት፤ በጋራ መከባበር የምትጸና የኅብረ ብሔራዊነት ታላቅ ቤት ናት !
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየንግድ ባንክ የበጎነት እጅ ለደብረ ብርሃን ወገኖች !
Next article