የንግድ ባንክ የበጎነት እጅ ለደብረ ብርሃን ወገኖች !

5
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብረ ብርሃን ዲስትሪክት የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ ለአቅመ ደካሞች የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
​ባንኩ “በአገልጋይነት እና በበጎነት!” በሚል መሪ መልዕክት ባከናወነው የበጎ አድራጎት መርሐ ግብር ከከተማዋ አምስት ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ 200 ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎች እገዛ ማድረጉን የተናገሩት የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር ሮቤል ጨቀር ናቸው።
ድጋፉ በነፍስ ወከፍ 50 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ 5 ሊትር የምግብ ዘይት እና ለዶሮ መግዣ የሚኾን ጥሬ ገንዘብ ነው ብለዋል። ባንኩ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን የመወጣት ተግባሩን በበዓላት ወቅት በዋናው መሥሪያ ቤት እና በሁሉም 33 ዲስትሪክቶች ደረጃ አጠናክሮ እያከናወነ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በተጨማሪም ዲስትሪክቱ በሚሸፍናቸው በከሚሴ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢዎች ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በስፋት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
​ባንኩ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን ከመወጣት ጎን ለጎን የአገልግሎት አሰጣጡን ዘመናዊ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት ከ1 ትሪሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ለመስጠት በጀት መድቦ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በደብረ ብርሃን ዲስትሪክት ሥር በሚገኙ 65 ቅርንጫፎች ደግሞ በየሩብ ዓመቱ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለማሰራጨት አቅዶ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት። ሌሎች ተቋማትም የባንኩን አርዓያነት በመከተል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በከተማው በርካታ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች መኖራቸውን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚሰጠው ቀልጣፋ አገልግሎት ባሻገር ለሚያደርገው ማኅበራዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ድጋፊ የደረሳቸው ወገኖች ባንኩ ያደረገላቸው እገዛ ለወገን ወገን ደራሽ መኾኑን በተግባር ያሳየ እንደኾነ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
✍️ ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በኅብር ቀን እንደጋገፋለን፣ እንተሳሰባለን” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)
Next articleኢትዮጵያ – የኅብረብሔራዊነት ታላቅ ቤት!