“በኅብር ቀን እንደጋገፋለን፣ እንተሳሰባለን” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

8
የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የኅብር ቀንን ምክንያት በማድረግ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሙያዎችን ተክተው ለደንበኞች አገልግሎት ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቺአምላክ ገብረማርያም መንግሥት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለዜጎች ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።
በክልሉ የመሶብ አንድ ማዕከል ከ63 ሺህ በላይ ደንበኞች አገልግሎት ማግኘታቸውንም አንስተዋል። አጠቃላይ በክልሉ ባሉ የመሶብ አንድ ማዕከላት ከ200 ሺህ በላይ ደንበኞች ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል። በአገልግሎት ደረጃም የኅብረተሰቡ እርካታ ከ99 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
በቀጣይ ሁሉንም አገልግሎቶች ወደ ማዕከሉ ለማስገባት እና አገልግሎቱን በሁሉም የአሥተዳደር እርከኖች ለማዳረስ ሰፊ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕርግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥትን አገልግሎት የበለጠ ለማዘመን የተዘረጋ አሠራር መኾኑን ተናግረዋል።
አገልጋይነትን፣ ምሥጋና እና ድጋፍን መሠረት በማድረግ የኅብር ቀን በክልሉ እየተከበረ መኾኑንም አንስተዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቁርጠኝነት እና የማመስገኛ ማዕከል ነው ያሉት አስተባባሪው ዕለቱ የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች ባለሙያዎችን ተክተው ለደንበኞች አገልግሎት የሚሰጡበት ቀን መኾኑን ነው የገለጹት።
አገልጋይነት የመደመር መንግሥት አንዱ መገለጫ በመኾኑ መሪዎች ከተገልጋዩ ጋር ፊት ለፊት የሚገናኙበት እና የተገልጋዩን ስሜት የበለጠ የሚያዳምጡበት መኾኑን ተናግረዋል። የኅብር ቀንን ደንበኞቻችን እያከበርን የአገልግሎት ቁርጠኝነታችን በተግባር የምናረጋግጥበት ዕለት ነው ብለዋል።
በክልሉ እስካሁን ስድስት የሚኾኑ ማዕከላት አገልግሎት ጀምረዋል። 10 ማዕከላት በመገንባት በቀጣይ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል።
መደጋገፍ እና መተባበር የአገልጋይነት እሴታችን ነው፤ በኅብር ቀን እንደጋገፋለን እንተሳሰባለን፣ እንተባበራለን፤ የመሶብ ተገልጋዮችም ኾነ አገልጋዮች አዲሱን ዓመት በተስፋ፣ በብርሃን እና በቁርጠኝነት የምንሠራበት ዓመት ይኾናል ነው ያሉት ።
በ2019 በጀት ዓመት የመሶብ አንድ ማዕከላትን እስከ ወረዳ በማስፋፋት ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለዜጎች ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠራም ተመላክቷል።
✍️ ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ኅብር በአንድነት በመቆም ለጠላት እሳት ለወዳጅ ብረት እንድንኾን ያግዛል” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next articleየንግድ ባንክ የበጎነት እጅ ለደብረ ብርሃን ወገኖች !