
በአማራ ክልል የማኅበራዊ ዘርፍ ስር የሚገኙ ተቋማት የኅብር ቀንን በተለያዩ መርሐ ግብሮች አክብረዋል። ቀኑ ለተማሪዎች ደብተር ድጋፍ በማድረግ፣ በደም ልገሳ እና በማዕድ ማጋራት ነው የተከበረው።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ዛሬ እየተከበረ የሚገኘው የኅብር ቀን ብዝኀነትን፣ አብሮነትን፣ አንድነትን እና የባሕል ውበትን የምናስብበት ቀን ነው ብለዋል።
የኅብር ቀን በአንድ ዓላማ በአንድ እሴት እና በመተባበር አብሮ መቆም የሚገለጽበት ቀን መኾኑንም አንስተዋል። በዚህም ልዩነታችንን አክብረን የሚያገናኙንን የጋራ እሴቶቻችን አጠናክረን ትብብርን፣ አንድነትን እና መተሳሰብን የምናስታውስበት ነው ብለዋል።
የቀኑ መከበር በልዩነቶች ሳይገደቡ ለሀገር ሰላም እና አንድነት በጋራ ቃል መግባትን መሠረት ያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ትስስር፣ ወንድማማችነት እና የጋራ አብሮነትን በማጉላት ለኢትዮጵያ አንድነት መሠረት ለመጣል ያለመ እንደኾነም ጠቁመዋል።
“የኅብር ቀን በአንድነት በመቆም ለጠላት እሳት ለወዳጅ ብረት ለመኾን ያግዛል” ብለዋል። የኅብር ቀንን አንድ ቀን ብቻ የምናከብረው ሳይኾን በዕለት ከዕለት የምንከተለው እና የምናከብረው የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መኾን አለበት ነው ያሉት።
ልዩነትን በማክበር፣ አንድነትን በማጠናከር እና ሰላምን በመጠበቅ በጋራ የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የኅብር ቀን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር እና የበጎነት እሴቶቻችንን በተግባር ለማሳየት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዚህም ማዕድ በማጋራት የዕርስ በርስ መደጋገፍን የምናድስበት ነው ብለዋል። የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፉ ለነገ ተስፋ የኾኑ ሕጻናት ልጆች መንገዳቸው የተሳካ እንዲኾን መሠረት የሚጥል መኾኑን አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
