
በደቡብ ጎንደር ዞን የጳጉሜን አራት የኅብር ቀንን ምክንያት በማድረግ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ተከብሯል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መንበር ክፍተው እንደገለጹት ድጋፉ ተማሪዎችን በፍጥነት ወደ ትምህርት ገበታቸው በመመለስ የተስተጓጎለውን የትምህርት ሂደት በአግባቡ ለማስቀጠል ትልቅ ትርጉም ያለው ነው።
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታ አሥራቴ ቀኑ የመተባበር እና የአንድነት እሴቶችን በማጠናከር ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ በማገዝ መከበሩ ለትምህርት ተቋማት መጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ወላጆች ቀደም ሲል በኢኮኖሚ እጥረት ምክንያት ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ይቆዩ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን የተደረገላቸው እገዛ ልጆቻቸው ያለ ሥጋት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸው መኾኑን ገልጸዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ብቻ ከ51 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
