🥼የሕይወትን ፈተና በጽናት እና በትምህርት ያሸነፉት መምህርት።

4

 

ጽናት በማይመች ሁኔታ እና በከበዱ ፈተናዎች ውስጥ እንኳ ሳይበገሩ ተስፋን ሰንቆ ወደፊት የመጓዝ ጥበብ ነው።

ወዲያውኑ የሚታይ ፈጣን ተአምር ሳይጠብቁ በየቀኑ በጸጥታ ድንጋይን እንደሚሸረሽር በማያቋርጥ የውኃ ጠብታ ዓይነት የውሳኔ እና የቁርጠኝነት ጥንካሬ ካለፉ ሰዎች መካከል መምህርት እንግዳወርቅ ገብረሥላሴ አንዷ ናቸው።

የቋንቋ መምህርት ናቸው። በደሴ ከተማ የምክር ቤት አባል እና የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትም ናቸው።ገና በልጅነታቸው ነበር የአካል ጉዳት (ዐይነስውርነት) የገጠማቸው። የዛሬውን ጥንካሬያቸውን ለመገንባት መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም።

ወታደር በነበሩት ታላቅ ወንድማቸው አርቆ አሳቢነት ገና በሰባት ዓመታቸው ነበር ቤተሰባቸውን ትተው ከደሴ ወደ ወላይታ ሶዶ ኦቶና ዐይነ ስውራን ትምህርት ቤት የገቡት።

በዚህ ሂደት የነበረባቸውን ፍርሃት ዛሬም ያስታውሱታል። ቀላል እንዳልነበረም አጫውተውናል። ሕይወት ግን እዚያው አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ የምግብ ዝግጅትን፣ የሙዚቃ መሳሪያዎችን እና የሕይወትን ጥበብ አሰናድታ አቆይታቸዋለች።

ከዓመታት በኋላም ከወላይታ ሶዶ ወደ ደሴ ሲመለሱ ደሴ ላይ የብሬል መጻሕፍት እጥረት እና የተዛቡ አመለካከቶች ብዙ መሰናክሎች ፈጥሮባቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ትግላቸው ግን አልቆመም። ጸንቶ ቀጥሏል።

ወንድማቸው ሁልጊዜም ከጎናቸው ነበሩ። እንደ አባት እና እናት ኾነው ይደግፏቸው፣ ለእርሳቸው ሲሉ በማያውቁት አካባቢ እስከ መደብደብ ዋጋ የከፈሉላቸው ወንድማቸው ለዛሬዋ እንግዳወርቅ የብርሃን መንገድ ጠራጊያቸው ነበሩ። ወንድም ጸንቶ ታናሽ እህትን ሲያጸና ምንኛ ደስ ይላል?

በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት፣ በመቀጠልም በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት መምህርት እንግዳወርቅ ከብዙ ውጣውረድ በኋላ በመምህርነት ሙያ ተሠማሩ።

ዛሬ ላይም የ25 ዓመታት የመምህርነት ልምድ ባለቤት ለመኾን በቁ። ራሳቸውን በሥራ ላይ አሰማርተው ግን እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም።

የደሴ ከተማ ምክር ቤት አባል በመኾን ከፊት ተሰልፈው የማኅበረሰባቸውን፣ የሴቶችን እና የአካል ጉዳተኞችን ድምጽ ያሰማሉ። አካል ጉዳተኞች የሥራ ዕድል፣ የቤት እና የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲኾኑ፣ ድምፃቸው እንዲሰማ እና አቅማቸው እንዲወጣም በትጋት ይታገላሉ።

“እኛን ማየት ምልክት ነው፤ ሴቶች ይችላሉ። አካል ጉዳተኝነት ከምንም ነገር አያግድም” ያሉን መምህርት እንግዳወርቅ በተለይም የሴት አካል ጉዳተኞችን ትምህርት እና ማኅበራዊ ድጋፍ ለማጠናከር በትጋት እየሠሩ ይገኛሉ። ሕይወት ያቀረበችላቸውን ፈተና በጽናት እና በትምህርት ያሸነፉት መምህርት እንግዳወርቅ ገብረሥላሴ ለአካላዊ ጉዳት ሳይበገሩ ከራስ አልፎ ለሀገር እና ለወገን መሥራት እንደሚቻል የጽናት ተምሳሌትነታቸውን አሳይተዋል።

#አሚኮ_ጽናት #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም

✍️በሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበበዓል ወቅት ከሚበዙ የዲጂታል ማጭበርበሮች ይጠንቀቁ!
Next articleሀገርን ለማጽናት እስከ መስዋዕትነት።