ከውድመት ወደ ማንሰራራት – አዲሱ የምዕራብ ጎጃም ገጽታ

12
የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ‘የማንሰራራት ቀንን በፍኖተ ሰላም እና ጅጋ ከተሞች የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በመጎብኘት አክብሯል።
ጉብኝቱ የንጹህ መጠጥ ውኃን በሶላር የመተካት፤ የጌጠኛ ድጋይ ንጣፍ፤ በጸጥታ ችግር የወደመ የቢሮ ዕድሳት፤ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የተከናወኑ የዲጂታላይዜሽን ተግባራት እና ሌሎችም ሥራዎች ይገኙበታል።
የጅጋ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ምስጋናው ድንቁ ከተማ አሥተዳደሩ ባለፉት የግጭት ዓመታት ካስተናገደው ውድመት በመውጣት የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከ32 ሚሊዮን በላይ ወጪ በማድረግ በግጭት ወድሞ የነበረውን ቢሮ በአዲስ መገንባት፤ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ችግርን የሚቀርፍ የሶላር ኃይል መትከል እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተገንብተዋል ነው ያሉት።
የምዕራብ ጎጃም ዞን መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ መምሪያ ኀላፊ ሙላት ፈረደ በሕዝብ መናኽሪያ ላይ ተገልጋዮችን ከእንግልት የሚታደግ እና አሠራሩን የሚያዘምን የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል። በዞኑ በዘጠኝ የሕዝብ መናኽሪያዎች ተግባራዊ እየተረገ ስለመኾኑ የጠቆሙት ኀላፊው ውጤታማ እንዲኾን የክትትል እና የቁጥጥር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ጌትነት ሙሉጌታ በበኩላቸው የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡን ያሳተፉ ተግባራት ተቀናጅተው እየተሠሩ ናቸው ብለዋል።
ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ያለውን የኮሪደር ልማትን ከፍኖተ ሰላም ከተማ ባሻገር በዞኑ አራት ከተሞች ላይ ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ንጉሥ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleማንሠራራት በእንጅባራ ከተማ ምን መልክ አለው?
Next articleባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን በመንገድ መሠረተ ልማት ስኬታማ ያደረጋት ምንድን ነው ?