
የእንስሳት ሀብት ልማቱን በማዘመን በኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን አወንታዊ ሚና ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር አስታውቋል። በከተማ አሥተዳደሩ የማንሠራራት ቀንን ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት ተክብሮ ውሏል።
ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ በግንባታ ላይ የሚገኘው ፉችታ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት፤ በኩታ ገጠም እየተሠራ ያለው የወተት ሀብት ልማት እና በተከታታይ ዓመታት በተሠሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እያገገመ ያለው የባሳ እንጓና ተፋሰስ ከተጎበኙ የልማት ሥራዎች መካከል ይገኙበታል።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ኑርልኝ ሰውነት ፕሮጀክቶቹ በኢኮኖሚ ማንሠራራት ላይ አወንታዊ ሚና የሚጫወቱ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለረጅም ዓመታት ትኩረት የተነፈገው የወተት ሀብት ልማትን ከተለምዷዊ አሠራር በማላቀቅ በተደራጀ እና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ሥራ አሥኪያጅ ዘላለም ዘውዱ በከፍተኛ ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘው ፉችታ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት አሁን ላይ ከ70 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በከተማዋ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ነው ያሉት። ፕሮጀክቱን እስከ ሕዳር 2019 ዓ.ም ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
