
የደቡብ ጎንደር ዞን እና የፋርጣ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ጳጉሜን ሁለት “የማንሥራራት ቀን” ምክንያት በማድረግ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
በዕለቱ በተካሄደው የጉብኝት መርሐግብር የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች ተጎብኝተዋል። አርሶ አደሮች የነበረባቸውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የተቋቋመው የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤት የጉብኝቱ አካል ነው።
የጉብኝቱ ተሳታፊ ሲሳይ አያሌው እንደገለጹት መድኃኒት ቤቱ አርሶ አደሮች አስፈላጊውን ሕክምና እና መድኃኒት በፍጥነት እንዲያገኙ በማድረግ የነበረውን አንገብጋቢ ችግር በብቃት ፈትቷል።
በተጨማሪም በሂደት ላይ የሚገኘው ባለ አራት ወለል የመሶብ አንድ ማዕከል ግንባታ ተጎብኝቷል። የፋርጣ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ይርጋ ጌትነት የግንባታ ሥራው አሁን ላይ 17 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ሲጠናቀቅ ኅብረተሰቡን በአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት እና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ከመኾኑም በላይ የአሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በደብረ ታቦር ከተማ አገልግሎት መስጠት የጀመረው አዲሱ መናኾሪያም ተጎብኝቷል። የደቡብ ጎንደር ዞን መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ መምሪያ ኀላፊ ዳግም ጥሩነህ የቀድሞው መናኾሪያ ይፈጥር የነበረውን ከፍተኛ መጨናነቅ እና የጉዳት ሥጋት አዲሱ መናኾሪያ መቅረፉን ተናግረዋል። ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ይህ የመንግሥት ሠራተኞች የጉብኝት መርሐ ግብር የኅብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግሮች እየፈቱ የሚገኙ ተጨባጭ የልማት ሥራዎችን በቅርብ ለመመልከት እና ለቀጣይ ሥራዎች አበረታች ምዕራፍ ለመፍጠር እንደሚያስችል ተጠቅሷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
