
በደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር አዘጋጅነት “የኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ መልዕክት ከዞኑ የመምሪያ ኀላፊዎች ጋር የዕመርታ ቀን የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
የምክክር መድረኩ የዞኑን እምቅ ሃብቶች በሳይንሳዊ መንገድ በማልማት እና ምርታማነትን በእጥፍ በማሳደግ በራስ አቅም ለመቆም የሚያስችሉ አዳዲስ ስልቶችን በመንደፍ ወደ ተግባር ለመግባት ያለመ ነው።
ከውይይት መድረኩ ጎን ለጎን በዞኑ የሚገኙ የማዕድን ምርቶች ለዕይታ የቀረቡ ሲኾን፣ የደቡብ ጎንደር ዞን ማዕድን ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ብርቄ ፀጋ ከዩኒቨርሲቲዎች የተገኙ ቀደምት ጥናቶችን በማቀናጀት እና አዳዲስ አካባቢዎችን በማጥናት የማዕድን ሃብቱን በባለሙያ ድጋፍ ለመጠቀም ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የዞኑ የመሬት ጥናት ባለሙያ ጌትነት አዲስ በበኩላቸው፣ ታሪካዊውን እና አጼ ቴዎድሮስ የሠሩበትን አካባቢ ጨምሮ በተደረጉ ቅኝቶች ሰፊ የብረት ማዕድን መኖሩ መረጋገጡን አብራርተው የታች ጋይንት የድንጋይ ከሰል ሃብትም አስፈላጊው ማረጋገጫ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ሀገራዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት የምርጥ ዘር እና የግብርና ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ የግብርና መምሪያ ኀላፊ የሽጥላ ፈቃዴ አስታውቀዋል። አክለውም በቀጣዩ ዓመት ዘመናዊ ሜካናይዜሽንን በስፋት በማስተዋወቅ ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የክልሉን የ10 ነጥብ 2 በመቶ የምርት ጭማሪ ግብ እውን ለማድረግ የክትትል እና የግምገማ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የፕላን እና ልማት መምሪያ ኀላፊ ዘመነ ውለታው ጠቁመዋል። በዞኑ የተጀመረው ይህ ሁለገብ እንቅስቃሴ የማዕድን እና የግብርና አቅምን በማቀናጀት ሀገራዊ ልማቱን ለማፋጠን በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
#አሚኮ #የማዕድንሃብት_ልማት #ደቡብጎንደር_አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
#ደብረ_ታቦር #ጳጉሜን_01_2018_ዓ_ም
ዘጋቢ፦ተክለብርሃን ፈንታ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
