በእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ለ173 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

7

 

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በመንግሥት በኩል ሰፊ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ዘርፍ አንዱ ነው።

በአማራ ክልልም የዘርፉን ጸጋ ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት አቅጣጫ ተይዞ እየተሠራበት ይገኛል።

የእመርታ ቀንን በማስመልከት የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ እና የሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በዘርፉ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ልዩ አማካሪ ይትባረክ አወቀ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ ውጤታማ የኾነ እና እመርታ የታየበት የእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከመደበኛው አሠራር በተጨማሪ ዘርፉን በአሠራር፣ በሰው ኀይል፣ በምርምር እና በፋይናንስ ለመደገፍ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሠጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

የእንስሳት ሃብት ልማቱን በኢንቨስትመንት በመደገፍ በጥራትም ኾነ በብዛት ተወዳዳሪ እንዲኾን መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) የእንስሳት ሃብትን በውጤታማነት በማልማት በሥርዓተ ምግብ ራስን ለመቻል ግብ ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል። በዚህም በከተማም በገጠርም ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን አብራርተዋል።

ተኪ ምርቶችን በማምረት በኩልም እያንዳንዱ ከተማ እና ወረዳ የሚጠቀመውን የእንስሳት ሃብት በራሱ እንዲችል ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራበት ስለመኾኑም ጠቁመዋል። ጥራትን በማሻሻል ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ ትኩረት ስለመደረጉም አብራርተዋል።

ዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝም አንስተዋል። በበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ173 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።

ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በ2018 በጀት ዓመት ከ2ነጥብ 7ሚሊዮን ቶን በላይ የወተት ምርት፣ ከ895 ሺህ ቶን በላይ የሥጋ ምርት፣ ከ43 ሺህ ቶን በላይ የዓሣ ምርት እንዲሁም ከ36 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ማምረት ተችሏል።

በ2019 በጀት ዓመት የታየውን እምርታ አጠናክሮ በማስቀጠል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በቅንጅት በመሥራት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግም ቢሮ ኀላፊው ተናግረዋል።

#አሚኮ #የእንሰሳትሃብት_ልማት #አማራክልል #ኢትዮጵያ

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_01_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከችግር ቆጣሪነት ወደ ድንቅ መዳረሻነት – የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሕዳሴ
Next articleበደቡብ ጎንደር ዞን ያለውን ሰፊ የብረት ማዕድን እና የድንጋይ ከሰል ሃብት ለማውጣት ጥረት እየተደረገ ነው።