ከችግር ቆጣሪነት ወደ ድንቅ መዳረሻነት – የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሕዳሴ

7

 

ኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባሕላዊ ጸጋዎቿ ሳይነኩ ለዓመታት ተቀምጠው የቱሪዝም ዘርፉም ለሀገር ዕድገት የሚጠበቅበትን ያህል ሳያበረክት ቆይቷል። ቀደም ሲል ሀገራችን በውጭው ዓለም በረሃብና በችግር ትርክት ብቻ ትታወቅ የነበረችበትን የተሳሳተ ገጽታ መቀየርም ትልቅ ፈተና ነበር።

ሆኖም ይህንን አካሄድ በአዲስ ዕይታ በመቀየር ዘርፉን የሀገሪቱ “አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር” ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት ቱሪዝም ከሀገራችን የብልጽግና ራዕይ ጋር ተናብቦ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያመጡ አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዓምዶች አንዱ ሆኖ ተለይቷል።

ዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ትክክለኛዋንና ውቧን ኢትዮጵያ ለዓለም ለማሳየት አይተኬ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

👉የታሪክና የተፈጥሮ ሃብቶችን ለአዲስ ትውልድ ማብቃት

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት የተተገበሩት ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ መርሐ ግብሮች የታሪክና የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ወደ ዘመናዊ መዳረሻነት በመገንባት ተጨባጭ እምርታ ማስመዝገብ ተችሏል።

👉የከተሞች መታደስና የኮንፍረንስ ቱሪዝም

በአዲስ አበባ የተገነቡት የአንድነት፣ እንጦጦና ሸገር ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንዲሁም ሰፊው የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ከተማዋን ለሰው ልጅ ምቹና የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል አድርገዋታል።

👉በክልሎች የተስፋፉ አዳዲስ መዳረሻዎች

ዛሬ ላይ እንደ ጎርጎራ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ሀላላ ኬላ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ቤኑና፣ ሀሮ ደንዲ እና ደንቢ ኢኮ ሎጅ ያሉ ውብ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም አድማስ በማግዘፍ አዲስ የለውጥ እምርታን ተመዝግቧል።

👉የቅርሶች ጥበቃና እድሳት

የብሔራዊ ቤተ መንግሥት (ኢዮቤልዩ)፣ የፋሲል አብያተ መንግሥታት፣ የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የሐረር ጀጎል ግንብ እድሳት ተደርጎላቸው የታሪክ እና ነባህል ጥልቀታችንን ለጎብኚዎች እያሳዩ ነው።

👉ዲጂታል አገልግሎት

“ቪዚት ኢትዮጵያ” (Visit Ethiopia) የተሰኘው የዲጂታል ፕላትፎርም መረጃዎችን በቀላሉ ለዓለም በማዳረስ ዘርፉን ዘመናዊ አድርጎታል።

👌በአኃዝ የተደገፈው የዘርፉ ስኬት

ይህ ታላቅ የልማት እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፍስሰት ማምጣት ችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) ዓለም በዚህ ዓመት ብቻ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የውጭ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን ከዘርፉም ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለሀገራችን መገኘቱን ገልጸዋል።

ዘንድሮ ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ጉብኝት በማድረግ ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ የሀገር ውስጥ የቱሪዝም የገንዘብ ዝውውር መፍጠር ስለመቻሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።

🌍 አቀፍ እውቅና

የተባበሩት መንግሥታት የቱሪዝም ማዕከል ኢትዮጵያ በ2025 እና 2026 በዓለም ፈጣን የቱሪዝም እድገት እያሳዩ ከሚገኙ ሀገራት መካከል በመመደብ ዕውቅና ሰጥቷታል።

የማኅበራዊ ሚዲያና ዲጂታል ማስተዋወቂያዎችም የሀገሪቱን በጎ ገጽታ ለዓለም በማሳወቅ ዘርፉ አይተኬ ሚና ተጫውቷል።

ለአብነትም እንደ አይሻው ስፒድ (IShowSpeed) እና እንግሊዛዊው ዲላን ፔጅ (Dylan Page) የመሰሉ ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የኢትዮጵያን መልካም ገፅታና ቱሪዝም ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከናወኑት የመሠረተ ልማት፣ የቅርሶች ጥገናና የተፈጥሮ መስህቦች ልማት ጥምረቶች ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው አህጉር ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ራዕይዋን በተግባር እያረጋገጡ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ጉዞ ከተዘጋ በር ወደ ዓለም አቀፍ መዳረሻነት በማሳደግ አስደናቂ እምርታ ተገኝቷል።

#አሚኮ #Ethiopiadelivers # Ethiopia
#ባሕርዳር ጳጉሜን 01/2018 ዓ.ም

ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleግብርናን ከኢንዱስትሪ አስተሳስሮ የቀጠለው የአማራ ክልል የእመርታ ጉዞ
Next articleበእንስሳት እና ዓሣ ሃብት ልማት ለ173 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።