
በአማራ ክልል ጳጉሜን 1 “የእመርታ ቀን” የአምራች ኢንዱስትሩዎችን እና በሰሜን ምዕራብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ግቢ በ28 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የበቆሎ ልማት እና የዶሮ እርባታን በመጎብኘት ተከብሯል። ጉብኝቱ የተካሄደው በክልሉ ግብርና፣ ገቢዎች፣ ገንዘብ፣ ማዕድን፣ ፕላንና ልማት፣ ኢንድስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮዎች የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች ነው።
የክልሉ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ተፈሪ ታረቀኝ እንዳሉት በ2018 በጀት ዓመት 3 ሺህ 961 ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ መሳብ ተችሏል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙና ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸውን የሴራሚክ፣ የወረቀት፣ የመድኃኒት፣ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ፣ የብረታ ብረት፣ የአሉሚኒየም እና ሌሎችም 174 መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ገብተዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ 194 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲያስገኙ የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካት ደግሞ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ችለዋል። በኢንዱስትሪው እና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ከ100 ሺህ በላይ ለኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
በ2019 በጀት ዓመትም አምራች ኢንዱስትሪው የሀገር ውስጥ ምርት ያለውን ድርሻ እንዲያሳድግ እና የኑሮ ውድነትን እንዲያረጋጋ፤ የፋይናንስ እና የግብዓት አቅርቦት ድጋፎችን በማጠናከር የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ታቅዷል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው በተለይም በሰብል ልማቱ ዘርፍ አስደናቂ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑን ተናግረዋል።
በበቆሎ እና በአኩሪ አተር የሚሸፈነው የማሳ መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። በዚህ ዓመትም በጥቅል 205 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
የምርት ዕድገቱ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ አግሮ-ኢንዱስትሪዎችን ከግብርናው ጋር በማስተሳሰር ጥራት እና መጠን ያለው የጥሬ ዕቃ ግብዓትን በስፋት ለማቅረብ ያለመ ነው።
የክልሉ የግብርና ከጥራጥሬና ቅባት እህሎች በተጨማሪ አቮካዶ፣ ማንጎ እና ቡና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኤክስፖርት አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
#አሚኮ #Ethiopiadelivers #Ethiopia
#ጳጉሜን01/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
