
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በማዕድን ልማት ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች።
ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ በዘመናዊ መንገድ በመጠቀም የኢኮኖሚዋ ምሰሶ ለማድረግ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው።
የዘርፉን ተወዳዳሪነትና ግልጸኝነት ለማሳደግ የወጡ አዳዲስ አዋጆችና ደንቦች ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል።
የሕጋዊ ወርቅ የማምረት አቅም ማደጉና ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ ሥራ መግባታቸውም ከፍተኛ የምርት መጠን እና የውጭ ምንዛሬ ገቢ አስገኝቷል።
በሀገሪቱ የሚገኙ ግዙፍ የማዕድን ፕሮጀክቶች ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለሀገር ውስጥ ገበያ ትልቅ ተስፋን ሰንቀዋል።
ሕገ-ወጥ የድንበር ማዕድን ዝውውርን ለመቆጣጠርና የሃብት ብክነትን ለማስቀረት ዘመናዊ የዲጂታል ክትትልና የቁጥጥር ሥርዓቶች ተዘርግተው እየተተገበሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የኾኑ እንደ ኦፓል፣ ፕላቲኒየም፣ ታንታለም፣ ፖታሽ እና ሊቲየም ያሉ ውድ የተፈጥሮ ማዕድናትን የታደለች ናት።
ኾኖም ከዚህ እምቅ ሀብት የሚገኘው ጥቅም ለረጅም ዘመናት በሕገ-ወጥ ንግድ፣ በኮንትሮባንድ፣ በቢሮክራሲ፣ በመሠረተ ልማት ችግርና ሥርዓት ባልያዘ ባሕላዊ አሠራር ተዳፍኖ እና ሲበዘበዝ ቆይቷል። ዛሬ ላይ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በአዲስ ዕይታ ዘርፉ ከነበረበት ውድቀት በመላቀቅ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ዋልታና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር መኾን ችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በ2018በጀት ዓመት በአንድ ዓመት ከወርቅ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ማሳካት መቻሉን አንስተዋል። ይህም የሚጨበጥ እና የሚዳስስ እምርታዊ ለውጥ ነው ብለዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጆነር ሀብታሙ ተገኘ የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ ለውጦች የታየበት ነው ብለዋል። የውጭ ምንዛሬ እያደገ መጥቷል። በዘረፉ የውጭ ባለ ሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ አስችሏል፤ በሥራ ዕድል ፈጠራም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማዳን እና የሀገር ውስጥ ምርትን ለመተካት ሥራ እየተሠራ ነው። በተለይም የአርጆ የድንጋይ ከሰል ፋብሪካን ጨምሮ ሌሎች ፋብሪካዎች በመገንባታቸው ከውጭ ይገባ የነበረውን ምርት በመተካት 300 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል። የኖራ ድንጋይ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ እና የስሚንቶ ምርት እንዲያድግም አግዟል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሶማሌ ክልል በኦጋዴን በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ ማምረት የሚችል ፕሮጀክት የተገነባ ሲሆን፣ 3 ነጥብ3 ቢሊዮን ሊትር የሚያመነጭ የተጣራ የጋዝ ማጣሪያ ፕሮጀክትም ተጨምሯል።
የማዕድን ዘርፉ በአሁን ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለኾኑ ኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ በርካታ ዜጎችም ኑሯቸው በዚህ ዘርፍ ላይ የተመሰረተ እንዲኾ አስችሏል።
በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፍ ከወጪ ንግድ ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል። በቀጣይ ዓመት ገቢውን ወደ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል።
#አሚኮ #Ethiopiadelivers #Ethiopia
ጳጉሜን01/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
