በዓላት ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው!

9

 

የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የክረምት የአደባባይ በዓላት የማጠቃለያ መርኀ ግብር በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በዓላትን ማክበር የመዝናኛ እና የመደሰቻ ብቻ ሳይኾን የማንነት፤ የታሪክ እሴቶችን፤ የትውልድ ቅብብሎሽን የሚያሳዩ መንገዶች ናቸው ብለዋል።

ክብረ በዓላት ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ የሚያገናኙ ድልድዮች መኾናቸውን ተናግረዋል። የበዓላት መከበር የባሕል ልምድን ለመጠበቅ፤ ለማጎልበት፤ የልጃገረዶችን ተሳትፎ ለማጠናከር፤ የሴቶችን ባሕላዊ ሚና ለማክበር እና የቱሪዝም ሃብት የኾኑት በዓላት ትውፊታቸው ተጠብቆ እንዲዘልቅ ጠቀሜታው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ የክረምት ወቅት የልጃገረዶች የነጻነት፣ የአብሮነት እና የባሕል ማሳያ የኾኑ በዓላት በድምቀት የሚከበሩበት ልዩ ጊዜ ነው ብለዋል።

ክብረ በዓላት የቱሪዝም መስህቦች መኾናቸውን ተናግረዋል። ባሕልን እንደ ታላቅ ሃብት ማየት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ቱሪዝም የሥራ ዕድል መፍጠሪያ፤ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ እና የገቢ ምንጭ መኾኑንም አንስተዋል።

ወጣቶች የሕዝብ መገለጫ በጎ ባሕሎችን ወደ ዲጂታል ዓለም ልታመጡት ይገባል ነው ያሉት። የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የተከበሩ የባሕል እሴቶችን ከዘመናዊው የዴሞክራሲ ባሕል ጋር ማስተሳስር ይገባል ነው ያሉት። በዓላት እና ባሕላዊ ሥርዓቶች የጋራ ማንነትን ያጠናክራሉ፤ ትውልድን ከትውልድ ያስተሳስራሉ፤ የፍቅር እና የመከባበር እሴቶችን ያስተላልፋሉ፤ የጋራ ታሪካችንንም በሕያው መልኩ ያስቀጥላሉ ነው ያሉት። በዓላትን በአንድነት እናክብር፣ በጋራ እንድመቅ፣ በመከባበር አንድነታችንን እናጠናክር ብለዋል።

#አሚኮ #Tourism #ኢትዮጵያ
#ባሕር_ዳር#ጳጉሜን _01_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

Previous articleየክረምት በዓላት የአዲስ ዓመት የብሥራት ምልክት ናቸው።
Next articleተቀብሮ የቆየው የማዕድን ሃብት ዕምርታዊ ለውጥ