የክረምት በዓላት የአዲስ ዓመት የብሥራት ምልክት ናቸው።

8

 

የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የክረምት የአደባባይ በዓላት የማጠቃለያ መርኀ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ መልእክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕላችን የአማራነት እና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መልክ ነው ብለዋል።

ባሕላችን ሳይበረዝ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በአንድነት ስናከብር ልዩነታችንን በማራቅ የጋራ እሴታችንን የምናጠነክርበት ነው ብለዋል። በአንድነት ማክበራችን አንድነታችን የጠነከረ መኾኑን ያሳያል ነው ያሉት።

በክልሉ ልዩነትን የሚፈጥር አንድም ነገር ሊኖር አይገባም ብለዋል። ባሕርዳር ከተማ የሁላችንም ቤት ናት በቆይታችሁ ደስተኛ እንደኾናችሁ ተስፋ አደርጋለሁም ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ የአማራ ክልል የቀደምት ሥልጣኔ አሻራዎችን የያዘ፤ የርካታ ቅርሶች እና የመስህብ ቦታዎች መገኛ፣ የልዩ ልዩ ባሕላዊ ክዋኔዎች መገኛ እና ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ክልል ነው ብለዋል፡፡

አሮጌው ዓመት ሲገባደድ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ደብረ ታቦር (ቡሄ)፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ፤ከሴ አጨዳ እና አሱሪቴ የነሐሴ ወር ጸጋዎች፤ የማኅበረሰቡ የተስፋ ማሳያዎች እና ስጦታዎች መኾናቸውን ተናግረዋል።

የክረምት በዓላት የአዲስ ዓመት የብሥራት ምልክት ናቸው ብለዋል።

በበዓላቱ ልጃገረዶች እና ወጣቶች በባሕላዊ አልባሳት አምረው፣ በእልልታ ታጅበው ሕያው ዜማዎችን የሚያዜሙበት፤ ጎዳናዎችን የሚያደምቁበት፤ የሴቶች ነጻነት እና ማኅበራዊ ክብራቸው በጎላ ሁኔታ የሚታይበት መኾኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የአደባባይ በዓላት የመደጋገፍ፤ የመተባበር፤ የጋራ ሕልውና፣ የጽናት እና የዘላቂ ስላም ዋነኛ ምሰሶዎች ኾነው ቆይተዋል ነው ያሉት።

በዓላት በጎ ተግባራት የሚያከናውነባቸው፤ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት፤ በኀዘን ላይ የሚገኙ የሚጽናኑበት፣ የታመሙት የሚጎበኙበት፤ ዘመድ እና ጎረቤት በፍቅር የሚገናኙበት ታላቅ የማኅበራዊ ትሥሥር መድረክ ናቸው ብለዋል፡፡

እኒህን ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ይዘታቸው ሳይቀየር፤ ክዋኔያቸው ሳይበረዝ፣ መልእክታቸው ሳይቀነስ፤ ለምተው እና ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

#አሚኮ#ባሕልና_ቱሪዝም#ኢትዮጵያ🇪🇹
#ባሕር_ዳር#ጷግሜ_01_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁን!

Previous articleየአማራ ክልል የክረምት የአደባባይ በዓላት የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
Next articleበዓላት ትናንትን ከዛሬ፤ ዛሬን ከነገ የሚያገናኙ ድልድዮች ናቸው!