🇪🇹 የኢትዮጵያ የእመርታ ጉዞ ወዴት?

12

 

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በይፋ ኃይል ወደ ማመንጨት ተሸጋግሯል። ይህም የኢትዮጵያን የውኃ ላይ ዲፕሎማሲ እና ውስጣዊ የመፈጸም አቅም በተግባር ያረጋገጠ ነው። የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ ጂኦ-ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትርክት የቀየረ ታሪካዊ ክስተትም ኾኗል።

የሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ወደ ኃይል ማመንጨት መሸጋገሩን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ይተገበራሉ ያሏቸው የ30 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶችን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በጉባ የተበሰሩት ፕሮጄክቶች ሀገሪቱን ከግብርና-መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ፣ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ፣ የማዕድን እና የሎጂስቲክስ ማዕከልነት ለማሸጋገር ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው።

እነዚህ ግዙፍ ፕሮጄክቶች ሀገሪቱን ከዝግመት ወደ ፍጥነት፤ ከጥገኝነት ወደ ሉዓላዊነት፤ ከችግር ወደ ብልጽግና ለማሻገር በቀላሉ የሚታዩ አይኾንም።

🛢️ የነዳጅ ማጣሪያ እና የጋዝ ፋብሪካዎች

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ እና ለነዳጅ ተዋጽኦ ምርቶች የምታወጣው የውጭ ምንዛሬ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ ሲፈታተነው ቆይቷል።

የነዳጅ ማጣሪያ መገንባት እና የጋዝ ፋብሪካዎችን (1ኛውን አስመርቆ 2ኛውን መጀመር) እውን ማድረግ፤ የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ግብዓትን በራስ አቅም ለመሸፈን ትልቅ ሚና ይጫወታል።

በዓመት 111 ሊትር ማምረት የሚችለው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጄክት የመጀመሪያው ዙር ተመርቋል፤ የሁለተኛው ምዕራፍ ሥራም እየተከናወነ ነው።

👉 የኒውክለር ማበልጸጊያ (ማመንጫ)

ይህ እጅግ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚጠይቅ እና ኢትዮጵያን በአፍሪካ የቴክኖሎጂ ልዕልና እንድትቀዳጅ የሚያደርግ ዕቅድ ነው። የኒውክለር ቴክኖሎጂ ለሰላማዊ ዓላማ (ለሕክምና፣ ለእርሻ እና ለተጨማሪ ኃይል ማመንጫ) ጥቅም ላይ መዋሉ ሀገሪቱ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድገዋል። ፕሮጄክቱን ዕውን ለማድረግም ከሩስያ መንግሥት ጋር ውይይት ተደርጓል፤ ስምምነትም ተፈርሟል። የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኮሚሽን ተቋቁሞም ሥራ ጀምሯል።

✈️ የቢሸፍቱ አየር ማረፊያ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ቁጥር አንድ አየር መንገድ ቢኾንም የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የመሸከም አቅም እየጠበበ መጥቷል። በአፍሪካ ትልቁን አየር ማረፊያ መገንባት ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ አቪዬሽን፣ የካርጎ እና የሎጂስቲክስ እምብርት ያደርጋታል። ይህ ፕሮጀክት የቱሪዝም ፍሰትን ከማሳደግ ባሻገር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንደ ቁልፍ ማነቃቂያ ያገለግላል።

🌾 የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ

የኢትዮጵያ ግብርና ዋነኛ ማነቆ የኾነው የማዳበሪያ እጥረት እና የዋጋ ንረት ነው። ፋብሪካውን በሀገር ውስጥ መገንባት የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና አርሶ አደሮችን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚደረግ የህልውና እርምጃ ነው።

ፋብሪካው በዓመት ሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የማምረት አቅም ይኖረዋል። ግንባታውን በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅም የግንባታ ስምምነት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ኩባንያ መካከል ተፈርሟል። ይህም ለኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ ኾኗል።

🏘️ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ

ፈጣን የከተማ መስፋፋት ባለባት ሀገር የመኖሪያ ቤት እጥረት ዋነኛ የማኅበራዊ እና የፖለቲካ ቀውስ መንስኤ ነው። ይህ ግዙፍ የቤት ልማት ፕሮጀክት የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት አምራች ኢንዱስትሪዎችን (ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ቀለም) በከፍተኛ ፍጥነት የሚያሳድግ የኢኮኖሚ ሞተር ነው።

🚀 በአጠቃላይ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የተቀየሱ የዘመኑ የዕድገት ሞተሮች ናቸው። የ”እመርታ ቀን” መንፈስም እነዚህን ግዙፍ ውጥኖች ከራዕይ ወደ ተግባር በመቀየር ኢትዮጵያን ከውጭ ጥገኝነት ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እና ልዕልና የሚያሻግራት አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ነው።

#Ameco #MegaProjects #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_01_2018_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባለፉ ዓመታት ምን ምን እምርታዎችን አስመዘገበች?
Next articleየአማራ ክልል የክረምት የአደባባይ በዓላት የማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።