
የኢትዮጵያ ጤና ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በፖሊሲ፣ በመሠረተ ልማት እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትግበራ ከፍተኛ ለውጥ አስመዝግባለች። ከተመዘገቡት ለውጦች መካከልም፦
📌የእናቶችና ሕፃናት ጤና ማሻሻል አንዱ ነው። እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ ከአምስት ዓመት በታች የሕፃናት ሞት መጠን ከ70 በመቶ በላይ በመቀነሱ ኢትዮጵያ ከዚህ አኳያ የልማት ግቦችን አስቀድመው ካሳኩ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትኾን ማድረጉን የዩኒሴፍ እና የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያስረዳሉ።
በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እና የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
📌መሠረታዊ የጤና አገልግሎትና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በሽታ ቅነሳ ላይም እምርታ ታይቷል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት የኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) በጋራ መከላከል ፕሮግራም መረጃ በኤች.አይ.ቪ (ኤድስ) በአዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እና በበሽታው የሚመዘገበው የሞት መጠን ከ90 በመቶ በላይ ቀንሷል። ከጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አኳያም በሺህ የሚቆጠሩ ባለሙያዎችን በማሠልጠን መሰረታዊ አገልግሎትን እስከ ገጠር ድረስ ማድረስ ተችሏል ።
📌የመድኃኒት ምርት እና ዲጂታል አቅርቦት ላይም እምርታ ታይቷል። ከሀገር ውስጥ ምርት አኳያ የመድኃኒት ማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ተገንብቷል። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲም (EPSS) ብክነትን የሚቀንስ የዲጂታል መከታተያ ሥርዓት ዘርግቷል።
📌 የወረርሽኝ መከላከል አቅም ላይም እድገት ታይቷል። ከቅድመ ጥንቃቄ አኳያ በኮቪድ-19፣ በኮሌራ፣ በፖሊዮ፣ በማርበርግና ሌሎችም በሽታወች በተስተዋሉበት ወቅት ኢትዮጵያ ባሳየችው የመከላከል አቅም እውቅና ማግኘቷንም የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ የክትባት ዘመቻዎችም ውጤት ተመዝግቦበታል።
📌 የጤና መሰረተ ልማት እና የሰው ኀይልም እድገት ማሳየቱን ከጤና ሚኒስቴር ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል። የኅብረተሰብ አቀፍ የጤና መድህን የዜጎችን የሕክምና ወጪ አቅልሏል። የሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ቁጥር አድጓል። በቀጣይም ጥራት ያለው እና ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተዳራሽ ማድረግ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በተለያዩ ጊዜዎች ሲናገሩ መደመጣቸው የሚታወስ ነው።
📌 ከላቁ ሕክምናዎች እና ሜጋ ፕሮጀክቶች አኳያ
በስፔሻላይዝድ ሕክምና ደረጃ የልብ ቀዶ ሕክምና፣ የኩላሊት ንቅለ-ተከላ እና የካንሰር የጨረር ሕክምና በቅዱስ ጳውሎስ እና በታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች በሀገር ውስጥ እየተሰጡ ይገኛሉ። ይህም የጤና ዘርፉ እድገት ለሀገር ብልጽግና እና ለዜጎች አምራችነት ወሳኝ መኾኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር) የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ.ር)ን ዋቢ አድርጎ የወጣው ይኽው የጠቅላይ ሚንስቴር ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደ ልብ እና የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ያሉ የላቁ ሕክምናዎች በሀገር ውስጥ መጀመራቸው የዜጎችን እንግልትና የውጭ ምንዛሬ ወጪ የሚቀንስ ታሪካዊ እርምጃ መኾኑን ይገልጻሉ። በጤናው ዘርፍ እየተሠሩ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዳሉም መረጃው አክሏል። ከእነዚህ መካከል የላቀ የሕክምና ማዕከል ግንባታ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ማስፋፊያ እና የኤሌክትሮኒክስ የህክምና መዝገብ (EMR/Telemedicine) ትግበራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
#አሚኮ #EthiopiaDelivers #Ethiopia
#ጰጉሜን 01/2018 ዓ.ም
ዘጋቢ-ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
