📜 የቀደምት አባቶች የጥበብ ቋጠሮ – ጳጉሜን የኢትዮጵያ የሥነ-ፈለክ ሕያው ምስክር

8

 

ጳጉሜን በዘመናት ሽክርክሪት መካከል ጊዜ የራሱን ጉዞ አቁሞ ትንፋሽ የሚሰበስብባት ከዓመታት ዑደት ያፈተለከች ረቂቅ ቀመር ናት።

የኢትዮጵያ 13ኛዋ የጸጋ ወር በቀናት ስሌት ውስጥ የምትገኝ ተራ ቁጥር አይደለችም። አሮጌው ዓመት ገና ሙሉ በሙሉ ሳይሰናበት፤ አዲሱም የብርሃን ድንኳኑን ሳይተክል በሁለቱ መካከል የተንጠለጠለች ድልድይ ናት።

📜 ዓለም በራሱ የጊዜ ቀመር ሲገሰግስ ኢትዮጵያ ግን በዚህች ልዩ የጸጋ ስጦታዋ የጊዜን ትርጉም በኪነ-ጥበብ ዳግም ትጽፋለች። የተረፈች የምትመስል ግን ደግሞ የዓመቱ ማሟያ የኾነችው ጳጉሜን በአብዛኛው አምስት ቀናት ቢኖሯትም በአራት ዓመት አንዴ ስድስት የመኾን ዕድል አላት።

♾️ በቀደሙት አባቶች ሕያው የዘመን ስሌት ቀመር እና በአንድሮሜዳ መጻሕፍ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠውም ከ282 ዓ.ም በኋላ ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም በመለየት ጳጉሜን ሰባት ቀናትን ይዛ ትውላለች። ቀኖቿ ግን የሚለኩት በሰዓታት ሳይኾን በውስጣቸው ባዘሉት ጥልቅ የዕድሳት መንፈስ ነው።

12ቱ ወራት ተጉዘው ሲያበቁ ጠፈር የክረምቱን ከባድ ካባ ለማውለቅ፣ ምድርም የብርሃን ዘውዷን ለመድፋት በዚህች አጭር እና ምስጢራዊ የጊዜ ኮሪደር ውስጥ በጸጥታ ያልፋሉ።

🌅 ጳጉሜን በቀደምት አባቶቻችን ጥልቅ የሥነ-ፈለክ ዕውቀት የተቋጠረች፣ የኢትዮጵያን የዘመን ስሌት ፍልስፍና ከትውልድ ትውልድ የምታስተላልፍ ሕያው ምስክር ናት። ይህች 13ኛዋ ወር የአላፊነት እና የዘላለማዊነት መገናኛ፣ የክረምት እና የበጋ ድንበር ማስመሪያ ድልድይም ናት።

✨ በጳጉሜን ረቂቅ የጊዜ ገበታ ላይ የትናንትናው ሸክም ሲራገፍ የነገው ብሩህ ተስፋ በንጹሕ ልብ ይጸነሳል። ይህች የዘመን መሸጋገሪያ ምስጢራዊ ፊደል የሰው ልጅ ዳግም ተስፋ እና ሌላ ብሩህ ዓመት የሚወጥንባት ናት። ተፈጥሮ ራሷን የምታነጻባት፣ ምንጭ እና ጅረቶች ኩልል ብለው ጠርተው የሚንፎለፎሉባት፣ ጋራና ሸንተረሩ በአበቦች የሚያሸበርቅላት እና ብርሃን በጊዜ ማሕጸን ውስጥ በጸጥታ የሚዘራባት የኢትዮጵያ የጥበብ ቋጠሮ ኾና ትዘልቃለች።

#Ameco #ጳጉሜን #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_01_2018_ዓ_ም

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“የሀገራችንን ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባን እንገኛለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባለፉ ዓመታት ምን ምን እምርታዎችን አስመዘገበች?