አካል ጉዳተኞችን ወደ ኋላ የሚያስቀራቸው አካል ጉዳታቸው ሳይኾን ምቹ ያልኾነ አካባቢ እና አግላይ አሠራር ነው።

10

 

የአማራ ልማት ማኅበር ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች እና ልማት ማዕከል ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የአጋርነት ስምምነት ተፈራርመዋል።

የአማራ ልማት ማኅበር ምክትል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ማሩ ወንዲፍራው ማኅበረሰቡ በራሱ አቅም ችግሮቹን መፍታት እንዲችል በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

የአባላቱን ቁጥር 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ያደረሰው ማኅበሩ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በአጋርነት በመሥራት ላይ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች እና ልማት ማዕከል ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ማድረጉን አቶ ማሩ ጠቁመዋል። የዚሁ አጋርነት አካል የኾነው ይኸው ስምምነት “ብቁ ወጣት” በተሰኘው መርሐግብር አማካኝነት የሚተገበር ነው።

80 በመቶ ወጣቶች የኾኑትን ሴት የአካል ጉዳተኞችን ጨምሮ የሌሎችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ለማሳደግ እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ አቅም እንደሚኾን ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች እና ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ስምኦን (ዶ.ር) ፕሮጀክቱ ማኅበረሰቡ ግጭትን፣ መፈናቀልን፣ የአየር ንብረት ለውጥን እና ድህነትን እየተጋፈጠ ባለበት በዚህ ወቅት ይፋ መኾኑን አንስተዋል። በተለይም አካል ጉዳተኛ ወጣቶች እና ታዳጊዎች የባሰ ተደራራቢ ጫና እና መገለል እንደሚገጥማቸው አብራርተዋል።

ዳይሬክተሩ አካል ጉዳተኞችን ወደ ኋላ የሚያስቀራቸው አካል ጉዳታቸው ሳይኾን ምቹ ያልኾነ አካባቢ እና አግላይ አሠራር ነው ብለዋል። በመኾኑም ይህ ፕሮጀክት የሥነ-ልቦና ድጋፍን፣ አካታች ትምህርትን፣ የደጋፊ ቴክኖሎጂ አቅርቦትን እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ተቋሙ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያካበተውን ልምድ በመጠቀም ከአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል። ሥራውም “ስለ እኛ ያለ እኛ ምንም” በሚለው አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ ማናቸውም ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች፣ ውሳኔዎች በሚቀረጹበት እና በሚተገበሩበት ወቅት በቀጥታ በሙሉ ባለቤትነት እና በውሳኔ ሰጭነት እንዲሳተፉ ይሠራል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በግጭት እና በመፈናቀል በተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ እንደሚተገበርም አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቱ ስኬት በተቋማት ቅንጅት ላይ የሚወሰን መኾኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። በመኾኑም መንግሥት፣ ማኅበረሰቡ፣ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና የልማት አጋሮች በጋራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሚኮ #ADA #ECDD #DisabilityRights #PartnershipForChange

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_29_2018_ዓ_ም

✍️ ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየዓባይ ነገር – ወዲህ ለሕልውና፣ ወዲያ ለከንቱ ሴራ
Next articleሳፋሪኮም በአማራ ክልል እና የርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መልእክት