የዓባይ ነገር – ወዲህ ለሕልውና፣ ወዲያ ለከንቱ ሴራ

16

 

ኢትዮጵያ በገዛ ተፈጥሯዊ ሀብቷ የመጠቀም ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብቷን በማረጋገጥ የገነባችው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የድህነት ታሪኳን የመቀየሪያ የመጀመሪያው ምዕራፍ እንጂ የማጠቃለያው ግብ አይደለም።

የዓባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውኃው ከኢትዮጵያ ተራራዎች የሚነሳ በመኾኑ ሀገሪቱ ወንዙን ለልማቷ እና ለሕዝቦቿ ብርሃን የማዋል እና ፍትሐዊ የመጠቀም መብቷ በፍጹም ሊደራደሩበት የማይችሉት መሠረታዊ እውነታ መኾኑን የዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።

ግብጽ የዓባይን ውኃ በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎቷን ለማሳካት እና ኢትዮጵያ በድህነት ውስጥ ተዘፍቃ እንድትኖር የተለያዩ ሴራዎችን ለዘመናት ስትጎነጉን ቆይታለች።

ግብጽ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እንዳታድግ እና ብሔራዊ ጥቅሟን እንዳታስከብር የተጠቀመችው የዲፕሎማሲ ጫና፣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ዛሬ ላይ ሙሉ በሙሉ ከንቱ ኾኖ ቀርቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ምሕንድስና መምህሩ ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ እንደሚያስረዱት ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ ገና መጠቀም ጀመረች እንጂ የማንንም ጥቅም አልነካችም፤ የዓባይ ወንዝ 45 ሺህ ጊጋ ዋት ኀይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም ያለው ሲኾን ኢትዮጵያ በግልጽነት እና በሕጋዊ መንገድ ወንዙን ለሌሎች የልማት አገልግሎቶች ፍትሐዊ በኾነ መልኩ የመጠቀም ሙሉ መብት አላት።

ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ ከጋዜጣ ፕላስ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የግብጽ ጩኸት የውኃ መጠን ቀንሶባት ሳይኾን ቀደም ሲል የነበራት በበላይነት ብቻ የመጠቀም ፍላጎቷ እንዳይኮላሽ ከመስጋት የመነጨ ነው” ብለዋል።

በተመሳሳይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውኃ ሃብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ኤልያስ ገበየሁ (ዶ.ር) ግብጽ ኢትዮጵያ ከድህነት ከወጣች የዓባይን ውኃ ሙሉ በሙሉ ትቆጣጠራለች በሚል ፍርሃት ልማቷን ለማደናቀፍ ስትጥር መቆየቷን ገልጸዋል።

ነገር ግን ግብጽ ኢትዮጵያን የመከልከል፣ የማገድም ኾነ የማስጠንቀቅ ምንም ዓይነት ሕጋዊም ኾነ ሞራላዊ መብት የላትም ነው ያሉት።

በዓባይ ወንዝ ላይ የኢትዮጵያን የልማት እውነታ መጋፈጥ ያቀታት ግብጽ አሁን ላይ ትኩረቷን ወደ ቀይ ባሕር ቀጣና በማዞር አዲስ የጂኦ-ፖለቲካዊ ትንኮሳ መስመር ለመክፈት እየሞከረች ትገኛለች።

ዶክተር ኤልያስ እንደሚሉት ግብጽ በዓባይ ጉዳይ ላይ የገጠማትን ሽንፈት ለመሸፈን እና የኢትዮጵያን ቀጣይ ዕድገት ለማሰናከል የምታደርገው ጥረት ፍጹም አይሳካም። በዓባይ ላይ የታየው ሀገራዊ ጥንካሬ በሌሎች የልማት እና የጂኦፖለቲካዊ ጉዞዎች ላይም ይደገማል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ስትገነባ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት (ግብጽ እና ሱዳንን) ለመጉዳት ወይም ውኃ ለመከልከል ሳይኾን በጨለማ ውስጥ የሚኖረውን ከ60 በመቶ በላይ ሕዝቧን የብርሃን እና የልማት ጥማት ለማርካት ነው ብለዋል።

የዓባይ ወንዝ የታችኞቹን እና የላይኞቹን ሀገራት በጋራ ማልማት እና መጠቀም የሚያስችል የተፈጥሮ ጸጋ መኾኑን በተደጋጋሚ አንስተዋል።

የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ በሴራ፣ በዛቻ እና በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ለማስቆም የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ውጤት እንደማያመጣ እና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ መንገድ በጽኑ መሠረት ላይ ኾና እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ምሁራን ሳይንሳዊ እና እውነተኛ አጀንዳዎችን በመቅረጽ የኢትዮጵያን ፍትሐዊ እና ተፈጥሯዊ መብት ከማሳወቅ ባሻገር ብሔራዊ ጥቅሟን ለዓለም ማኅበረሰብ ማስገንዘብ እና የሀገሪቱን የልማት ጉዞ ማስቀጠል እንዳለባቸውም ተመላክቷል።

#አሚኮ #ብሔራዊ_ጥቅም #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_29_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleበደቡብ ጎንደር ዞን ሰላምን ሲያውኩ የነበሩ ጽንፈኞች ተደመሰሱ።
Next articleአካል ጉዳተኞችን ወደ ኋላ የሚያስቀራቸው አካል ጉዳታቸው ሳይኾን ምቹ ያልኾነ አካባቢ እና አግላይ አሠራር ነው።