
ኢትዮጵያን እናፈርሳለን፤ አማራን እናጠፋለን ብሎ የተነሳው ሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ባደረገው ወረራ በአማራ ክልል አካባቢዎች ዘርፈ ብዙ ግፎችን መፈጸሙ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በይፋ መገለጹ ይታወሳል።
ይህ ሕገ ወጥ ቡድን የአማራን ሕዝብ እና ሀገርን በጠላትነት ፈርጆ እና በወረራ ይዞ የዘር ማጥፋት በትሩን ካሳረፈባቸው አካባቢዎች መካከል ጭና አንዷ ናት። ቡድኑ በጦርነት ማሸነፍ ሲያቅተው በቀሉን ለመወጣት በቤት ውስጥ የተገኘውን ንጹሐን ሁሉ አሰቃየ፤ ሲያበላው ሲያጠጣው የቆየውን ከድቶ፣ የበላበትን ወጭት ሰብሮ የጅምላ ጭፍጨፋውን ፈጽሟል። የቁም እንስሳትን ጨምሮ የሕዝቡን ሀብት ንብረት ዘርፏል።
የተረፈውንም አውድሟል። ጭና ላይ ይህን በተግባር ፈጽሟል። በወቅቱ በጭና ጭፍጨፋ ከሞት የተረፉት የዐይን እማኞች እንደገለጹት በዚህ ጭፍጨፋ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ እናቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ያለ ልዩነት በግፍ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በሕገ ወጡ የሕወሃት ቡድን የጭካኔ ድርጊት ጭና የደም ምድር ኾኖ አልፏል። “ጭና የደም ምድር የጅምላው መቃብር…”።
አስከፊው የጭና ጭፍጨፋ ድርጊት በታሪክ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። የጭና ጭፍጨፋ ሰለባዎችም በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ።
ይህ አይነት ጥቁር ታሪክ እና መጥፎ ጠባሳ በየትኛውም አጋጣሚ ዳግም እንዳይደገም ማድረግ የዚህ ዘመን ትውልድ የቤት ሥራ ነው።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
