በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገነባው ሙዚየም የኢትዮጵያን የፍትሕ ሥርዓት በዲጅታልና በቁስ ሰንዶ የያዘ ነው።

17
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተገበራቸው ካሉ የተቋምና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና የዘመናዊ ዳኝነት አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ በተጨማሪ የሀገሪቱን እና የክልሉን የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ከጥንታዊ አሠራር እስከ ዘመናዊው ሥርዓት የሚዳስስ የፍትሕ ሙዚየም ግንባታ ይገኝበታል።
ለሙዚየሙ የሚሆን ዘመናዊ ሕንጻ ከመገንባት እስከ ማደራጀት እና ለጎብኝዎች ክፍት ማድረግ በርካታ ሂደቶችን አልፏል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ።
ሙዚየሙ ርዕሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ እና ሌሎችም መሪዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ ለጎብኝዎች ክፍት ሆኗል።
በመረሀግብሩ ላይ የሙዚየሙን መገንባት እና መደራጀት አስፈላጊነት ለእንግዶቹ ያስረዱት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው፣ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓቱ የሀገሪቱ ታሪክ አንድ አካል መሆኑን ገልጸው ፣ ይህንን ታሪክ አደራጅቶ ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ ትውልዱ የሀገሪቱን የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ከጅማሮው እስከ አሁን ድረስ መረዳት እንዲኖረው ታስቦ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሙዚየሙን ለማደራጀት ዘመናዊ ሕንጻ ከመገንባት ጀምሮ፣ ለሙዚየሙ ግብዓት የሚሆኑ ታሪካዊ ሰነዶችን፣ መዛግብትን፣ የፎቶ፣ የድምጽ እና የቁሳቁስ ግብዓት ለመሰብሰብ እና ለማደራጀት ከክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጨምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሌሎች የሥራ ክፍል ኀላፊዎችን ያካተተ ቡድን ተቋቁሞ ዓመቱን ሙሉ ሲሠራ መቆየቱን አብራርተዋል።
ሙዚየሙ በሀገሪቱ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓት ላይ ምርምሮችን ለሚያካሂዱ ተመራማሪዎች፣ የሕግ ተማሪዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች በማጣቀሻነት የሚያገለግሉ የሰነድና የምስል ክምችቶች አሉት። ለፖሊሲ እና ሌሎች የዳኝነት እና የፍትሕ ስትራቴጂክ ሰነዶች ዝግጅት የሚያገለግሉ ግብዓቶች የሚገኙበት ማዕከልም ነው ብለዋል።
የፍትሕ ሙዚየሙ በከፊል ዲጂታል ሆኖ የተደራጀ ሲኾን፣ የሕግ ተማሪዎች እና እጩ ዳኞች የሚለማመዱበት ምስለ ችሎት ጨምሮ መደበኛ ችሎት መከታተል የሚችሉበትን የዲጂታል አገልግሎት የያዘ ነው። ሙዚየሙ ከነሐሴ 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።
ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ሙዚየሙ ተመራማሪዎቻችን በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ ታሪክ ውስጥ ያለፈውን ረጅም ሂደት በአንድ ቦታ ላይ ለማግኘት ያስችላቸዋል” መንገሻ አየነ (ዶ.ር)
Next articleየጭና ግፍ እና የትውልድ የቤት ሥራ