“ሙዚየሙ ተመራማሪዎቻችን በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ ታሪክ ውስጥ ያለፈውን ረጅም ሂደት በአንድ ቦታ ላይ ለማግኘት ያስችላቸዋል” መንገሻ አየነ (ዶ.ር)

6
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት እና የፍትሕ አካላትን ታሪክ ጠብቆ ለማቆየት፣ በፍትሕ ዘርፉ ተሳታፊ ለሆኑ ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ ፖሊስ፣ ጠበቆች እና የሕግ ተማሪዎች የእውቀት ምንጭ የሚሆን፣ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት በማሕበረሰብ ግንባታ ላይ ያላቸውን ሚና ማኅበረሰቡ እንዲረዳ የሚያስችል እና እምነት የሚያሳድግ፣ ለተመራማሪዎች የግብአት ምንጭ የሚሆን፣ ትውልድ የፍትሕ ሥርዓት ከየት ጀምሮ የት እንደደረሰ እንዲረዳ የሚያስችል የፍትሕ ሙዚየም አደራጅቶ ለጎብኝዎች ክፍት አድርጓል።
በሙዚየሙ ውስጥም፦
👉 ፍትሐ ነገሥትን ጨምሮ የመጀመሪያ የተጻፈ ሕገ መንግሥት፣
👉 የመጀመሪያ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ማቋቋሚያ ሕጎች ፣ ቀደምት ውሳኔዎች፣ ፎቶዎች እና አልባሳቶች የያዘ ሲሆን፣
👉 የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ምስለ ችሎት የሚያካሂዱበትን አዳራሽ ጨምሮ ሌሎች ከዳኝነት እና ከፍትሕ ሥርዓቱ ጋር የተያያዙ ታሪካዊ ቁሳቁሶች ይገኛሉ።
በሙዚየሙ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር)፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የገነባው የፍትሕ ሙዚየም ” ህያው ላይብረሪ”መሆኑን ጠቅሰው፣ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጋር በአጋርነት እና በትብብር ለሚሰራው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የሙዚየሙ መገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ሙዚየሙ ተማሪዎቻችን እና ተመራማሪዎቻችን እንደ ሀገር በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ ታሪክ ውስጥ ያለፈውን ረጅም ሂደት በአንድ ቦታ ላይ ለማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል።
ይሄንን ማድረግ የነበረባቸው ዩኒቨርስቲዎች ነበሩ ያሉት ዶክተር መንገሻ፣ ትክክለኛ መሪዎች ተቋማትን ይገነባሉ፣ ይህንን ላደረጉ የተቋሙ መሪዎች አመሰግናለሁ ብለዋል።
ለመማር ማስተማሩ እና ለምርምር ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተናገሩት ዶክተር መንገሻ አየን፣ የሙዚየሙ መገንባት እና ሥራ መጀመር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ የመረጃ ግብዓት መሆኑን ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምን ያመለክታል?
Next articleበአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተገነባው ሙዚየም የኢትዮጵያን የፍትሕ ሥርዓት በዲጅታልና በቁስ ሰንዶ የያዘ ነው።