የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምን ያመለክታል?

18
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት እስከ 2027 የሚቆይ “ብርቱ” ኤል ኒኖ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ቢቢሲ እንደዘገበው ይህ ክስተት ዓለምን ወደ ከፋ የሙቀት አደጋ ያሸጋገራታል።
የፓስፊክ ውቅያኖስ የውኃ ወለል ሙቀት እስከ 4 ዲግሪ ሴልሺየስ ይጨምራል። ከወለሉ በታች ያለው ደግሞ እስከ 8 ዲግሪ ያድጋል። ይህም አደጋውን ከ1950 ወዲህ ከተመዘገቡት ሁሉ የከፋ ያደርገዋል።
በአኹኑ ወቅትም ተጽዕኖው ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ኤስያ እና አውስትራሊያ ድረስ በከፍተኛ ኹኔታ እየታየ ይገኛል።
✍️እያደረሰ ያለው ተጽዕኖ!
#በአውስትራሊያ፦ የባሕር ሙቀት ማዕበል የባሕር ሕይወትን ጎድቷል፤ የወፎች ጉንፋን፣ የአልጌ ማበብ እና የዓሦች እልቂት አስከትሏል።
#በደቡብ ምሥራቅ ኤስያ እና ማዕከላዊ አሜሪካ፦ ድርቅ እና የደን ቃጠሎ ተስፋፍቷል። በኢንዶኔዥያ ከ107 ሺህ ሄክታር በላይ ደን ተቃጥሏል።
#ፓናማ ቦይ፦ በድርቅ እና በውኃ መጠን መቀነስ ምክንያት የመርከቦች እንቅስቃሴ ከ10 በመቶ በላይ ቀንሷል።
#ቻይና፦ እስከ 7 የሚደርስ ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች (ታይፉኖች) ይከሰታሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቀደም ባሉት አውሎ ነፋሶች የሰው ሕይወት አልፏል፤ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል ተብሏል።
#ደቡብ አሜሪካ፦ በደቡብ ብራዚል ከፍተኛ ዝናብ እና ጎርፍ ይጠበቃል። በፔሩ እና ኢኳዶር የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ በመኖሩ አሜሪካ የሕክምና መርከብ ወደ ፔሩ ልካለች።
✍️በምሥራቅ አፍሪካ፦
#ድርቅ እና የዝናብ እጥረት አካባቢዎች፦ በኤል ኒኖ ወቅት የሰሜን፣ የሰሜን ምዕራብ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ክረምት ጥገኛ የኾኑ የሰብል አምራች ቦታዎች፣ ኤርትራ እና የሱዳን ክፍሎች የዝናብ እጥረት፣ የሰብል ውድመት እና ድርቅ ያጋጥማቸዋል።
#የከባድ ዝናብ እና የጎርፍ አካባቢዎች፦ በሌላ በኩል ደቡብ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ኡጋንዳ ደግሞ ከወትሮው በተለየ ከባድ ዝናብ (በተለይ ከመስከረም መጨረሻ እስከ ታኅሣሥ መጨረሻ ባለው ጊዜ ዝናብ ወቅት)፣ የጎርፍ አደጋ እና የመሬት መንሸራተት ያጋጥማቸዋል።
ከባድ ዝናብ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት፣ ​​መንገድ፣ ድልድይ እና የመኖሪያ ቤቶችን ያፈርሳል። ​የኮሌራ እና የወባ በሽታዎችን ሥርጭት ይጨምራል።
​የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት የቅድመ ማጠንቀቂያ መረጃዎችን እያሠራጨ ነው። የጤና ሥርዓት፣ የመጠለያ እና የንጹህ ውኃ መሰረተ ልማት እጥረት አደጋውን የከፋ ሊያደርገው እንደሚችልም አስጠንቅቋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሕ ሙዚየም ያየነው ሥራ ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ ለብዙዎች መነሳሳት ይሆናል” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)
Next article“ሙዚየሙ ተመራማሪዎቻችን በዳኝነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ ታሪክ ውስጥ ያለፈውን ረጅም ሂደት በአንድ ቦታ ላይ ለማግኘት ያስችላቸዋል” መንገሻ አየነ (ዶ.ር)