“በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፍትሕ ሙዚየም ያየነው ሥራ ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ ለብዙዎች መነሳሳት ይሆናል” በለጠ ሞላ (ዶ.ር)

11
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር)፣ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ቢሮ ውስጥ የተገነባውን የፍትሕ ሙዚየም እና የፍርድ ቤቱ በቴክኖሎጂና በዳኝነት አገልግሎት ዘርፍ ያከናወናቸውን ሥራዎች ተመልክተዋል። የፍትሕ ሙዚየሙን መጎብኘታቸው የሀገሪቱን የፍትሕ ታሪክ ለመረዳት ትልቅ ዕድል እንደሰጣቸው ገልጸዋል። በተለይም ፍርድ ቤቱ ያከናወናቸው የቴክኖሎጂ ልማትና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች እጅግ የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ፍርድ ቤቱ የተገበረው የቴክኖሎጂ ሥራ በሀገር ደረጃ የወጡ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች በተቋማዊ ደረጃ በምን ያህል መልኩ ወደ ተግባር ሊቀየሩ እንደሚችሉ ያሳየ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በተለይም የፍትሕ ታሪክ መዛግብትን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ የዲጂታል ዳኝነት መሠረተ ልማቶችን መዘርጋት፣ ግልጽና የርቀት ክርክር የሚካሄድባቸውን ዘመናዊ የችሎት አዳራሾች መገንባት፣ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን እና የጥሪ ማዕከልን ማደራጀት የፍርድ ቤቱ የለውጥ ሥራ ዋና መገለጫዎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
“ሥራው የሀገር አቀፍ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በምን ያህል ደረጃ እየተተገበሩ እንዳሉ ያሳየ ነው” ያሉት ዶክተር በለጠ፣ ለዚህ የቴክኖሎጂ ዝርጋታና የታሪክ መዛግብት የዲጂታላይዜሽን ሥራ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን፣ በተለይም ከፍተኛ አመራሩን አመስግነዋል።
ሚኒስትሩ በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ የተገበራቸው ወረቀት አልባ የዳኝነት አገልግሎቶችና ሌሎች የለውጥ ሥራዎች የዳኝነት አገልግሎትን ከማዘመን ባለፈ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ያየነው ሥራ ከክልሉ አልፎ በሀገር ደረጃ ለብዙዎች መነሳሳት እንደሚሆን አልጠራጠርም” ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የፍትሕ ሙዚየሙ የተመረቀው የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ነው። ከምረቃ መረሃ ግብሩ በተጨማሪ፣ የፍርድ ቤቱ የዲጂታላይዜሽን መሠረተ ልማቶች፣ ዘመናዊ የችሎት አዳራሾች፣ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትና የጥሪ ማዕከል ጨምሮ ሌሎች የተቋሙ የለውጥ ሥራዎች ተጎብኝተዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዲጂታል ዳኝነት፣ በታሪካዊ መዛግብት ጥበቃ እና በዳኝነት አገልግሎት ማዘመን ያከናወናቸው ሥራዎች ለሌሎች የፍትሕ ተቋማት ተሞክሮ ሊኾኑ እንደሚችሉ በሥነ ሥርዓቱ ተገልጿል።
ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከውኃ ሥር የሚበቅለው ነጭ ወርቅ
Next articleየዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምን ያመለክታል?