
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ “ኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሠረት” በሚል መሪ መልዕክት የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የፓናል ውይይት አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ዲጂታል 2025 ስትራቴጅን ተግባራዊ በማድረግ የሕዝብ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ያደረገችው ርብርብ ተጨባጭ ፍሬን አፍርቷል ብለዋል።
የመንግሥት ተቋማት ከወረቀት አሠራር ወጥተው ወደ ዘመናዊ የዲጂታል አሠራር እየተሸጋገሩ መኾኑንም ተናግረዋል። ከ49 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት በመኾን፤ ዜጎች በቴሌ ብር እና በባንኮች በዲጂታል መድረኮች በመገበያየት እና በመሶብ አገልግሎት ፈጣን ተጠቃሚ ኾነዋል ነው ያሉት።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን እውን ለማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷልም ብለዋል። ተደራሽነትን ማስፋት፤ ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር፤ በዜጎች እና በተቋማት መካከል እምነትን ማጠናከር የዲጂታል 2030 የትኩረት አካል መኾናቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ያዘጋጀው አውደ ርዕይ የተቋማትን የዲጂታል ግንዛቤ ለማሳደግ፤ የፈጠራ ሥራዎችን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የመንግሥት አጀንዳ ብቻ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ሕዝብ እና መንግሥት የሚገናኙበት እውነተኛ መንገድ መኾኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል መሠረተ ልማትን ማግኘት ቅንጦት አይደለምም ብለዋል። ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሁሉም ተጠቃሚዎች በእኩልነት የሚያገለግል አድሎ አልባ ድልድይ መኾኑንም አንስተዋል።
ወጣቶች በእጃችሁ የያዛችሁት ስማርት ስልክ መዝናኛ ብቻ ሳይኾን የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት በመኾኑ በአግባቡ ልትጠቀሙበት ይገባል ነው ያሉት። የሚመጣው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን የሚፈልገው ወጣቶችን በመኾኑ ራሳችሁን ከአዲሱ ቴክኖሎጂ ጋር ልታላምዱ ይገባል ብለዋል።
ቴክኖሎጂ መንግሥት ሠራተኛኞችን ለፈጠራ እና ለውሳኔ ሰጭነት የሚያበቃ በመኾኑ ቴክኖሎጂን መታጠቅ እና መላመድ ይገባል ብለዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ከዳር ለማድረስ በተቋማት መካከል ያሉ የዲጂታል መረጃ ቋቶች እርስ በዕርስ የሚናበቡበት እና በሕግ መሠረት መረጃ የሚለዋወጡበት ሀገራዊ ማዕቀፍ ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል።
እጅ ለእጅ ተያይዘን ትኩረታችንን በፈጠራ እና በግንባታ ላይ በማድረግ ልጆቻችን የሚኮሩባት ሀገር እንገነባለን ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
