
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ የበለጸጉ እና በሥራ ላይ የሚገኙ ችግር ፈች የኾኑ ሲስተሞችን በአውደ ርዕይ ለጎብኝዎች ክፍት አድርጓል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አውደ ርዕዩን አሥጀምረዋል። የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎችም ተገኝተዋል። በአውደ ርዕዩ “ኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሠረት” በሚል መሪ መልዕክት የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበትም የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ መንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ቴክኖሎጂን እንደ አካታች ሀገራዊ ብልጽግና፤ ዘላቂ ልማት እና ለብቁ ሀገራዊ ተወዳዳሪነት ቁልፍ መሠረት አድርጎ እየሠራበት ነው ብለዋል።
በኢኮኖሚ ዕድገት፤ ምርታማነትን በማሳደግ፤ በመንግሥት አገልግሎት ቅልጥፍናን በማሻሻል፤ የዜጎች ተሳትፎን በማሳደግ፤ የዲጂታል ክህሎትን በማጠናከር ግብ አድርጎ በትኩረት እየሠራ እንደኾነ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ልማት ለውጭ ኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አንስተዋል። በአማራ ክልል “ዲጂታል አማራ” በሚል በ25 ዓመቱ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ላይ ቴክኖሎጅ እንደ ልማት መዳረሻ መፍጠሪያ ተደርጎ ተይዟል ነው ያሉት።
በ25 ዓመቱ ስትራቴጅክ ግብ ላይ በ2042 የአማራ ክልል ዋነኛ ሀብት፤ የአገልግሎት መስጫ እና የኢኮኖሚ የዕድገት ምንጭ ቴክኖሎጂ እንዲኾን ይሠራል ነው ያሉት።
በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ቴክኖሎጂን የመጠቀም፤ የማላመድ እና የመሥራት ልምምዳቸውን እንዲያጠናክሩም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምድ ዕድገት እያሳየ መጥቷልም ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት ቴክኖሎጂን በስፋት ለመጠቀም በትኩረት እየሠራ ነውም ብለዋል።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እና ዜጎች በአገልግሎት ደስተኛ እንዲኾኑ እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው የመርሐ ግብሩ ዓላማ በአማራ ክልል የለሙ የዲጂታል መፍትሔዎችን በጋራ ለመመረቅ እና ወደ ሥራ ለማስገባት ነው ብለዋል።
በርካታ የለሙ ሲስተሞች ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል። ሌሎች የለሙ ሲስተሞችም ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል።
አውደ ርዕዩ የመንግሥት የአሠራር ሥርዓት ዲጂታላይዝድ እንዲኾን ለማፋጠን እና ዲጂታል 2030ን እውን ለማድረግ ያለመ ነውም ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ከ35 በላይ ዲጂታል መፍትሔዎች ለምተው ለተቋማት እና ለኅብረተሰቡ ክፍት መኾናቸውንም ገልጸዋል።
አውደ ርዕዩ አገልግሎት ሰጭው እና አገልግሎት ተጠቃሚው ስለ ዲጂታል መፍትሔዎች አውቆ እንዲጠቀም ለማድረግ እንደሚያስችልም ነው ያነሱት። የለሙ ሲስተሞች ለአገልግሎት ክፍት መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
