
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብን ጤና ለመጠበቅ መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱን ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት አምስት የስትራቴጅክ ግቦችን ቀርጾ ለኅብረተሰብ ጤና ስጋት የኾኑ በሽታዎችን በመከላከል እና በመቆጣጠር በኩል ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
በክልሉ የመውጫ እና መግቢያ በሮች ላይ ወረርሽኝ እንዳይገባ ቅኝት የማድረግ እና የመቆጣጠር ሥራዎች መሠራቱን ገልጸዋል። የላቦራቶሪ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱ እንዲያድግ በማድረግ እና በተደራጀ የመረጃ ትንተና በኩል ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የጤና ምርምርን በማጠናከር በኩልም አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል። በሽታዎችን በቤተ ሙከራ የመለየት፣ የመከታተል፣ ለጤና ተቋማት የቴክኒክ ድጋፍ የማድረግ ሥራዎችን መሠራቱን ነው የተናገሩት። “በበጀት ዓመቱ አበረታች የበሽታዎች ቅኝት እና የቁጥጥር ሥራዎች መሠራታቸውንም” አብራርተዋል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል የማኅበራዊ ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይነህ መላኩ በጤናው ዘርፍ አበረታች ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከክልሉ አልፎ ለሌሎችም ተሞክሮ የሚኾን የሕዝብን ጤና የመጠበቅ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
