ባሕር ዳርን ውብ እና ጽዱ ማድረግ የሁሉም ነዋሪዎች ኀላፊነት ነው።

15
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ፤ ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት የ2018/19 በጀት ዓመት የክረምት የበጎ ፍቃድ የጽዳት ዘመቻ መርሐ-ግብር ተካሂዷል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የጽዳት ዘመቻው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን መነሻ በማድረግ ባሕር ዳር ከተማን ውብ እና ጽዱ የማድረግ ዓላማ ይዞ መካሄዱን ተናግረዋል።
በዘመቻው እንደ ከተማ አሥተዳደር በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል። ሁለተኛ ወሩን በያዘው በከተማዋ የዜጎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተመዘገቡ በርካታ በጎ ፈቃደኞች በንቃት እየተሳተፉ መኾናቸውን አንስተዋል።
የተያዙ ተግባራትም በውጤታማነት እየተፈጸሙ መኾኑን አብራርተዋል። በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እስከ መስከረም 21/2019 ዓ.ም ይቀጥላል ያሉት ኀላፊዋ ቀሪ ተግባራትም በውጤታማነት ይተገበራሉ ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አካባቢ ጥበቃ ጽዳት እና ውበት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጽጌረዳ አበበ የጽዳት ዘመቻው ማኅበረሰቡ ተሞክሮውን በመውሰድ ለከተማዋ ጽዳት እና ውበት አጋር እንዲኾን በዐቢይ እና በቴክኒክ ኮሚቴ በጋራ የተካሄደ ነው ብለዋል።
ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ ውብ እና ጽዱ ባሕር ዳርን ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የጽዳት ዘመቻ የውኃ ማፋሰሻ ቦዮችን የማጽዳት፤ የ20/50 ሜትር ራዲየስ ሞዴል መንደር የመፍጠር፤ አረንጓዴ ተክሎችን የመትከል፤ መጤ አረሞችን የማስወገድ እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን አብራርተዋል።
ዘመቻው ለበጋው መደበኛ የጽዳት ተግባር አጋዥ እንደሚኾንም ተናግረዋል። በጽዳት ዘመቻው የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው ባሕር  ዳርን ውብ እና ጽዱ ማድረግ የሁሉም ነዋሪዎች ኀላፊነት ነው ብለዋል።
በዘመቻው ተሳትፎ ያደረጉትም ባሕር ዳር ጽዱ ስትኾን ተጠቃሚዎቹ ራሳችን ነን በሚል እሳቤ መኾኑን ገልጸዋል። የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል።
✍️ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleበአንድ ዓመት 553 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሳበው የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት
Next articleየበሽታዎች ቅኝት እና የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረዋል።