በአንድ ዓመት 553 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሳበው የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት

21
🔥
🚀
💰 3 ሺህ 961 አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ አማራ ክልል በመግባት 553 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ፈሰስ ያደረጉት በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ነው።
🏆 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ማምረት በማስገባት፤ የማምረት አቅማቸውን በማሳደግ፤ በተኪ ምርት እና በኤክስፖርት የውጭ ምንዛሬ በማዳን እና በማስቀረት ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ እንደገለጹት እነዚህ ስኬቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሁለተኛ ደረጃ እውቅና እና ሽልማትን አስገኝተዋል። አበረታች ውጤቱ ድንገት የመጣ ሳይኾን ከተቀናጀ የዕቅድ ትስስር እና አመራር የመነጨ እንደኾነም ገልጸዋል።
🚀 ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት እና አሠራርን ለማዘመን የተወሰደው ቁርጠኛ እርምጃም ስኬቱን ይበልጥ አፋጥኖታል። ኢንዱስትሪውን በብቃት የሚመራ ጠንካራ መዋቅር እና መሪ ለመፍጠር በተሰጡ ተከታታይ ሥልጠናዎች ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ባለሙያዎች የዘርፉን ወሳኝነት ጠንቅቀው በመረዳት በላቀ የሥራ ተነሳሽነት ወደ ተግባር በመግባት መሠራቱንም ተናግረዋል።
💻 አገልገሎትን ቀልጣፋ እና ከቢሮክራሲ ነጻ ለማድረግ በአንድ ማዕከል የኢንቨስትመንት አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ለስኬቱ አብነት አድርገዋል። አጠቃላይ አሠራሩን ዲጂታል የማድረግ የሪፎርም ሥራም እየተከናወነ ነው።
💪 ክልሉ ባለፉት ዓመታት ያሳለፋቸውን የጸጥታ እና የፖለቲካ ማነቆዎች፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ ያልዋሉ እምቅ የግብርና፣ የማዕድን እና የሰው ኃይል ጸጋዎች እንደ ትልቅ መነሻ መወሰዳቸውን ጠቁመዋል። መሪዎች ያለፈውን ጊዜ ለማካካስ በከፍተኛ እልህ እና ቁጭት ሌት ከቀን መሥራታቸው እና ከክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ጀምሮ ዘርፉ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ መደረጉ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
🌟 እነዚህን አቅሞች በአግባቡ በማቀናጀት ክልሉ ባጋጠሙት ፈተናዎች ውስጥም ኾኖ ከማንም ባልተናነሰ መልኩ አኩሪ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል በተግባር አሳይቷል። ይኸው ተሞክሮ ክልሉ ወደ ተሟላ እና የተረጋጋ ሰላም ሲሸጋገር ከዚህም በላይ በከፍተኛ ፍጥነት ሊመነጠቅ እንደሚችል ማሳያ መኾኑንም አንስተዋል።
🎯 በዘርፉ የተገኘውን ብሩህ ተስፋ እና የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ በ2019 በጀት ዓመት ክልሉን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ፣ የገቡ ፕሮጀክቶችን ምርታማነት ለማሳደግ እና የአምራች ኢንዱስትሪው በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ በላቀ ቁርጠኝነት እና ዝግጅት ወደ ሥራ መገባቱንም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮን አውደ ርዕይ አሥጀመሩ።
Next articleባሕር ዳርን ውብ እና ጽዱ ማድረግ የሁሉም ነዋሪዎች ኀላፊነት ነው።