“ሥራችሁን በአግባቡ ሥትሠሩ ሕዝብ ያመሠግናችኋል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

16
የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) “በ2018 በጀት ዓመት የፈጸምናቸውን የመንገድ፣ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ ሥራዎቻችን በጥልቀት እንገመግማለን፣ ውጤታማ ሥራዎችን አጠናክረን እናስቀጥላለን፤ በሂደቱ የታዩ ውስንነቶችን ደግሞ እናስተካክላለን” ነው ያሉት።
በክልሉ የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል። ዘርፉ አገልግሎት ያቀርባል፣ ያስተዳድራል፣ ያለማል ነው ያሉት። ዘርፉ በራሱም ዕድገት ተኮር ነው ያሉት ኀላፊው ለሌሎች ዘርፎችም የዕድገት መሠረት ነው ብለዋል። ለሌሎች ዘርፎችም የዕድገት መሠረት የኾነውን ዘርፍ በአግባቡ መምራት እና ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት ዘርፉ የኢኮኖሚ የደም ሥር መኾኑን በመረዳት ባለ ሁለት ፍኖት ዓላማ ይዞ እንዲደራጅ ማድረጉን ገልጸዋል። አገልግሎት የሚያቀርብ እና የኢኮኖሚ አሳላጭ እንዲኾን መደረጉንም ተናግረዋል። ያለ ሁለቱ ፍኖቶች ኢኮኖሚያውን ማሳደግ እንደማይቻልም ገልጸዋል።
ሕዝቡ ከዘርፉ ትልቅ ነገር ይፈልጋል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ለኢኮኖሚውም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ይጠበቃል ብለዋል። የተሳለጠ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አማራጭ የትራንስፖርት አቅርቦት ላይ ያለውን ክፍተት መሙላት እንደሚገባም ተናግረዋል። ሕገወጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ማስቆም እና ሕዝቡ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ ብቻ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የትራንስፖርት ዘርፉ ለሌብነት የተጋለጠ እንደኾነ ያነሱት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን እና ሌብነትን መከላከል ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት።
የሎጂስቲክስ ዘርፉም የምርት እንቅስቃሴ በአግባቡ እንዲሳለጥ፣ ኢኮኖሚያው ላይ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በትኩረት መምራት እንደሚገባም ገልጸዋል። በቀጣይ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።
መንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ የኢኮኖሚ የደም ሥር ናቸው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ መሪዎች ይሄን ተገንዝበው ምን አቀድን ? ምንስ አሳካን ? በማለት ለነገ ውጤታማ የሚያደርግ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የመንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ዘርፍ ብቻውን የቆመ አይደለም፤ በባሕሪው ከሁሉም ጋር የተሳሰረ ነው፤ ይሄን ባሕሪ ተረድቶ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። የሦሥተኛ ወገን ችግሮችን፣ የመንገድ ደኅንነቶችን፣ የሚፈጠሩ ሕገ ወጥ ተግባራትን መቆጣጠር እና በአግባቡ መምራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ሕዝብ የሚያነሳቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት ግዴታ እንደኾነም ገልጸዋል። መንገድን በጥራት እና በአጭር ጊዜ የመገንባት አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል። የመንገድ፣ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ መሠረተ ልማትን ማሻሻል እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ዘርፉ ያለውን የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል። “ሥራችሁን በአግባቡ ሥትሠሩ ሕዝብ ያመሠግናችኋል፣ ኢትዮጵያም ታመሠግናችኋለች” ነው ያሉት። ሀገር እና ሕዝብ እንዲያመሠግናችሁ እና ከዘርፉ የሚጠበቀው ውጤት እንዲገኝ በትኩረት መሥራት አለባችሁም ብለዋል።
#አሚኮ #መንገድ፣ ትራንስፖርትና_ሎጂስቲክስ_ቢሮ_የዕቅድግምገማ #አማራክልል
🇪🇹
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ በክልሉ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የድርሻውን እየተወጣ ነው” አቶ ዓባይ መንግሥቴ
Next articleበምርታማነት ማንሠራራት፤ የአማራ ክልል አዲስ የግብርና ጉዞ!