
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም፣ የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን የሚገመግም መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግርና የሥራ መመሪያ ያስተላለፉት የቢሮው ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ፤ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን መረጃ ለሕዝብ ከማድረስ ባሻገር በክልሉ ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት እንዲሰፍን ታሪካዊ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል። አክለውም በክልሉ ለተገኘው የሰላም አየርና ለሕዝቡ አብሮነት መጎልበት ዘርፉ ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱን አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተግባራት የዘርፉን ኃያልነት በተግባር ያረጋገጡ እንደነበሩ የጠቆሙት ኀላፊው፤ እነዚህ ሥራዎች የሕዝቡን የልማት እንቅስቃሴ የሚያፋጥኑ፣ እውነትን የሚያጎሉና የክልሉን መልካም ገጽታ በመገንባት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የተካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የተወጣው ሚና በታሪክ የሚዘከር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዘርፉ የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ የልማት ፍላጎት በማንጸባረቅ ረገድ የተጫወተው ሚና ለልማት ሥራዎች መፋጠን ትልቅ አቅም መሆኑንም አቶ ዓባይ አብራርተዋል።
በመድረኩ ያለፉትን ስኬቶችና ያጋጠሙ ማነቆዎችን በመፈተሽ፤ በቀጣይ የበጀት ዓመት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም፣ ወንድማማችነትና ሁለንተናዊ እድገት በላቀ ኃላፊነት እንዲሠራ መንገድ የሚጠርግ መሆኑ ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
