ያልተነጣጠሉት ሥጋ እና ነፍስ የሰላም እጦት ዋጋ እና የኢኮኖሚ ማገገም ተስፋ።

10
🔗
ሰላም እና ኢኮኖሚ ልክ እንደ ነፍስ እና ሥጋ የማይነጣጠሉ፣ አንዱ ያለአንዱ ሊቆሙ የማይችሉ የህልውና መሠረቶች ናቸው። ኢኮኖሚ ያለ ሰላም መሠረት እንደሌለው ቤት ሲኾን፤ ሰላምም ያለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በቀላሉ ሊፈርስ የሚችል ደካማ ጎጆ ነው።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች አጋጥሞ የነበረው የሰላም እጦት ይህንን ሀቅ በግልጽ አሳይቷል። ግጭቱ እና የመንገዶች መዘጋት ዜጎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ ከማድረጉም ባለፈ፤ የንግድ እንቅስቃሴ መገደቡን እንደ መልካም አጋጣሚ በተጠቀሙ ትላልቅ ነጋዴዎች አማካኝነት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነት ተከስቶ ሸማቹን ለከባድ ችግር አጋልጦ መቆየቱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው አንጻራዊ ሰላም ግን ነዋሪዎች ያለምንም ስጋት ወጥተው በመሥራት ኑሯቸውን እንዲመሩ እና የኢኮኖሚ መረጋጋት እንዲፈጠር ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ መኾኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የፊስካል ፖሊሲ ዳይሬክተር ጥላሁን ጀምበሩ የሰላም እጦት በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ጫና ዘርፈ ብዙ እና ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
📉💥 የሰላም እጦት አጥፊነት በዋጋ ንረት ላይ:-
እንደ ዳይሬክተሩ ግጭት ሲከሰት የምርት እና የአቅርቦት ሰንሰለት ይቋረጣል፤ አርሶ አደሩ ከማሳው ይፈናቀላል፣ የእርሻ ግብዓት ዝውውር ይስተጓጎላል፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም ይገታል። የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ሲቀንስ እና የምርት ወጭ ሲጨምር የዕቃዎች እጥረት ይፈጠራል፤ ይህ ቀጥታ ወደ ዋጋ ንረት ያመራል።
የዋጋ ንረቱ የዜጎችን የመግዛት አቅም በማዳከም የኑሮ ውድነትን ያባብሳል፣ ሥራ አጥነትን ያነግሳል፣ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲከሰት በማድረግ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን አደጋ ላይ እንደሚጥለው አስረድተዋል።
🧗‍♀️🌾 በቀውስ ወቅት መቋቋም:-
ቀውስ ሲከሰት ዋናው ትኩረት ኢኮኖሚውን ከመፍረስ መታደግ ላይ እንደኾነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ይህንን ለማድረግ የቅድሚያ ወጭ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ማሥተዳደር እንደሚገባ ነው የጠቆሙት። በተለይም የምግብ አቅርቦት እንዳይቋረጥ ለግብርናው ዘርፍ (ዘር እና ማዳበሪያ) በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።
🌱🚧 ከቀውስ በኋላ ማገገም እና መልሶ መገንባት:-
የእርዳታ ሥራን ብቻ ከማቅረብ ባለፈ የተጎዱ አካባቢዎችን እና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምን በመፍትሄነት አስቀምጠዋል። የግል ዘርፉን አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ችግር በማዳመጥ እና ጉድለታቸውን በመሙላት ማበረታታት፣ የመንግሥትን የገቢ መሠረት ዳግም ማስፋት ትኩረት የሚሹ ተግባራት መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
🕊️🪙 የሰላም እና ኢኮኖሚ ተመጋጋቢነት:-
ሰላም እና የሕግ የበላይነት መስፈን የዜጎችን በነጻነት የመኖር መብት ከማስፈኑም ባሻገር ለባለሀብቶች እና አልሚዎች አስተማማኝ ምህዳርን ይፈጥራል። አርሶ አደሩ ያለስጋት ሲያመርት እና ነጋዴውም ምርቱን በነጻነት ሲያዘዋውር ጤናማ የንግድ ሰንሰለት ከመፈጠሩም በላይ ሰፊ የሥራ ዕድል፣ ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነት እና ጠንካራ የመንግሥት አቅም እውን ያደርጋል።
ይህ የሚገነባው ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ሰላምን ይበልጥ ዘላቂ ስለሚያደርገው ሰላም ከደኅንነት ጉዳይነት ባሻገር የሀገር ዋነኛ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት ኾኖ ይቀጥላል።
ሰላም የሁሉም ዜጋ የጋራ ኀላፊነት በመኾኑ የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ እና የብልጽግና ጉዞን ዕውን ለማድረግ ሁሉም በቅንጅት እና በአንድነት መሥራት ይገባዋል።
ዘጋቢ: ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“የተሠሩ የልማት ሥራዎችን መጠበቅ የትውልዱ አደራ ነው”
Next articleየሃይማኖት ተቋማት ለሰላም እና አብሮነት