
በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ያስፈተናቸውን ሁሉንም ተማሪዎች ማሳለፉን አስታውቋል።
ተማሪ ጽዮን አንተነህ የ12ኛ ክፍል የሀገር አቀፍ ፈተናውን ከወሰዱ የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት። 559 ከ600 ውጤትም ማስመዝገብ ችላለች።
ይህን ውጤት ለማስመዝገብ በግል እና በቡድን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ለፈተና ሲዘጋጁ እንደነበር ነው የገለጸችው።
ሌላኛው የትምህርት ቤቱ ተማሪ ሱራፌል ተስፋዬ በፈተናው 544 ውጤት አስመዝግቧል። ጊዜውን በአግባቡ መጠቀሙ እና የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ ያደርግላቸው የነበረው ድጋፍ ለዚህ ውጤት እንዳበቃው ተናግሯል።
የትምህርት ቤቱ መምህራንም የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲሠሩ እና እንዲለማመዱ ከማድረግ ባለፈ በሥነ ልቦና ዝግጁ ኾነው ፈተና እንዲወስዱ ማድረጋቸው ለውጤት እንዳበቃቸው ተማሪዎቹ ተናግረዋል።
በተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት መደሰታቸውን ነው የገለጹት። ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነት እና የትምህርት ቤቱ መምህራን በብዙ ችግሮችም ውስጥ ኾነው ተማሪዎችን ውጤታማ እንዲኾኑ ያደረጉት ጥረት ለዚህ ውጤት እንዳበቃቸው ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ ባልተመቻቸ እና አስፈላጊ ግብዓቶች ሙሉ በሙሉ ባልተሟላበት ሁኔታ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ለቀጣይ ከዚህ በላይ ለመሥራት ትልቅ መነሳሻ ይኾናል ነው ያሉት።
የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ደረጀ ከፈለኝ በ2018 ዓ.ም ከተፈተኑ 37 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ውስጥ 28ቱ ከ500 በላይ ማስመዝገብ ችለዋል። በትምህርት ቤቱ 569 ከፍተኛ ውጤትም ኾኖ ተመዝግቧል ነው ያሉት።
ይህ ውጤት በመምህራን፣ በትምህርት ቤቱ አሥተዳደር እና በሌሎች አጋር አካላት ጥረት የተመዘገበ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ያስፈተናቸውን ሁሉንም ተማሪዎች ማሳለፉን የተናገሩት ርእሰ መምህሩ ትምህርት ቤቱ ባለፋት ሦስት ዓመታት ያስመዘገበውን ውጤት ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ በማስቀጠል የቀደመ ታሪኩን መድገሙን ገልጸዋል።
በቀጣይም አዳሪ ትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሥራውን በራሱ ተቋም እንዲጀምር ማድረግ፣ የመምህራንን ጥቅም ማሟላት እና ሌሎችም ግብዓቶች ተሟልተው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ባለሃብቶች፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ እና የሚመለከታቸው አጋር አካላት እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለ2019 የትምህርት ዘመን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ240 በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
