
የሰላምን አማራጭ በመቀበል በእንጅባራ ከተማ በከብት ማድለብ ዘርፍ ተሠማርቶ የሚገኘው የቀድሞው ታጣቂ ወጣት ያለፈውን አስቸጋሪ ጊዜ በመሰናበት ወደ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ሕይወት መሸጋገሩን ይናገራል።
ወደ መደበኛ ሕይወቱ የተመለሰው ወጣቱ አሁን ላይ የከብት ማድለብ ሥራውን በመጀመር የራሱን እና የቤተሰቡን ሕይወት በባለቤትነት እየመራ መኾኑን ገልጿል። ከመንግሥት የተደረጉለትን የተለያዩ ድጋፎች በመጠቀምም ሥራውን አጠናክሮ የገቢ ምንጭ ማግኘት መጀመሩን ገልጿል።
ከዚህ ቀደም ከነበረው የጥፋት መንገድ በመውጣት ሰላምን መምረጡ ሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዳመጣለት ነው የተናገረው። ከዚህ በፊት ለፈጠረው ስህተትም መቆጨቱን ነው የገለጸው። ሕይወትን ለማዳን ወደ ሰላም ጎዳና መመለስ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳሰበው የሰላም ተመላሹ በመንግሥት የተከፈተውን የሰላም በር በመጠቀም ማኅበረሰቡን መካስ እንደሚገባም አሳስቧል።
ለአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ እና የሰላም መንገድ በመምረጥ የቀድሞውን ስህተት በማረም በሰላም እና በፍቅር ማኅበረሰቡን ማገልገል ይገባል ነው ያለው።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ቢሻው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምን የማጽናት ሥራ ከሀገር ሽማግሌዎች፤ ከጸጥታ አካላት፤ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት መከናወኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ በመቀበል ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን ያስረዱት ኀላፊው ለተመለሱ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል። ወደ መደበኛ የመንግሥት ሥራቸው የተመለሱ እንዳሉም አንስተዋል። ሌሎች ደግሞ የሰላም ማስከበር ሥራውን በመቀላቀል የሕግ ማስከበር ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
በተለያዩ ከተሞች እና ወረዳዎች ለተመለሱ አካላት የንግድ ቦታዎች፣ የገንዘብ ድጋፍ እና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ተመቻችቶላቸዋል ብለዋል።
በዚህም በግብርና፣ በእንስሳት ማድለብ እና በዶሮ እርባታ ሥራዎች ተሠማርተው የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ መደረጉን ነው የተናገሩት።
የሰላም በሩ አሁንም ክፍት መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው የሰላምን አማራጭ ለሚከተሉ አካላት ከመንግሥት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እና ማቋቋሚያ እንደሚደረግም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
